እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን አይሲስ ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምስራቅ ማሊ ሜናካ ግዛት ውስጥ ለተፈፀመው ጥቃት ኃላፊነት ወስደ። ‘16 ወታደሮችን ገድያለሁ’ ብሏል።
ይሁንና የማሊው ወታደራዊ ገዥ ድንገቱን የተመለከቱ ዘገባዎች መሰማት ከጀመሩበት ካለፈው ሃሙስ አንስቶ እስካሁን የተናገረው የለም።
አይሲስ ‘አማክ’ በተሰኘው የፕሮፓጋንዳ አውታሩ አማካኝነት ባሰራጨው መልዕክት፣ ‘ከቡድኑ ጋር አጋርነት አላቸው’ ያላቸው ተዋጊዎች ወደ ኒዠር በመጓዝ ላይ የነበሩ የማሊ ጦር ሰራዊት አባላትን በደፈጣ መግደላቸውን ተናግሯል።
ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው ውጊያ ቁጥራቸው ወደ አስራ ሁለት የሚጠጋ ወታደሮች ቆስለዋል ሲልም አክሎ ገልጿል። ማሊ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2012 ዓም አንስቶ በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል የጀመረውን እና ወደ መሃል አገር የተስፋፋውን፤ ብሎም ወደ ጎረቤት ቡርኪናፋሶ እና ኒዠር የተዛመተውን የእስላማዊ ጽንፈኞች ጥቃት በመዋጋት ላይ ትገኛለች።
"ሜናካ" “እስላማዊው መንግሥት በታላቁ የሰሃራ ክልል” በእንግሊዝኛው ምሕጻረ ቃል ISGS የተባለው ቡድን ለወራት ያህል ዋናው የጦር ግንባሩ ያደረገው አካባቢ ነው።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ያወጣው ዘገባ “ከዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ ለተፈጸሙ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ግድያዎች እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ቡድኑን ተጠያቂ አድርጓል።
መድረክ / ፎረም