በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ መሪ ለሃገሮች መሪዎች አቤቱታ ፃፉ


የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ
የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ

የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት የገባውን አዲሱን የአውሮፓ 2017 ዓመተ ምህረት ምክንያት በማድረግ “በኤርትራ ላይ ቀጥሏል” ላሉት የፍትህ መዛባት በደል ዳግመኛ ትኩረት የሚስብ መልዕክት ለብዙ ሃገሮች መሪዎች ልከዋል።

ፕሬዚዳንቱ “የሚፈፀመው ኢፍትሃዊ ድርጊት አንድም ምንም ምክንያት ሊሰጠው የማይችል፤ አንድም መሠረታዊ የዓለም አቀፍ ህግጋትና የሞራል ደምቦችን የሚጥስ ነው። ከዚያ በላይ ደግሞ ለክልላዊ ፀጥታና ሰላም አደጋ የሚደቅን ነው” ማለታቸውን ከኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ አትቷል።

“የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ብይኑን ከሰጠ አሥራ አራት ዓመታት አልፈውም የኤርትራ ግዛቶች አሁንም በወረራ እንደተያዙባት ናቸው” ያሉት ፕሬዚደንት ኢሣያስ የሃገሮች መሪዎች የህግን የበላይነት ያስከብሩ ሲሉ ጠይቀዋል።

በሀገራቸው ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች “ህገ ወጥና ኢፍትሃዊ ናቸው” ሲሉ የኤርትራው ፕሬዚደንት አማርረዋል ።

“በተንኮልና በሃሰት በተፈበረከ ውንጀላና ሉዓላዊ ግዛታችን በወረራ ተይዞ በካሣ የማይወጡት በደል እየደረሰብን ነው” በማለት አስምረው “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጥፋቱን ፈጥኖ ያስተካክል” ሲሉ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ማዕቀቦቹ እንዲቀጥሉና የመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያና የኤርትራ ተቆጣጣሪ አካል ሥልጣን እስከዚህ 2017 ዓ.ም. ታኅሣስ አጋማሽ እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል ።

XS
SM
MD
LG