በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ ወታደሮች "በኢሮብ ግድያና ዝርፊያ ፈጽመዋል" ተባለ


Advocacy
Advocacy

የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ኢሮብ ወረዳ የሚገኙ 63 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውንና 58 ቤቶችን ማቃጠላቸውን ለኢሮብ ብሄረሰብ መብቶች መቆሙን የሚገልጸው Irob Advocacy Association የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስታውቋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአካባቢው ነዋሪም የኤርትራ ወታደሮች የካቲት 16 2013 ዓ\ም፣ በምስራቅ ትግራይ ዞን ወረዳ ሳዕስዕ ፃዕዳ እምባ ውስጥ፣ ስድስት ሰላማዊያን ሰዎችን መግደላቸውን ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ በርካታ የገበሬ ቤቶች በኤርትራ ወታደሮች መቃጠላቸውን የተመለከቱ መሆኑንም የዓይን ምስክርነታቸውን የሰጡት እኝሁ ግለሰብ ገልጸዋል። የትግርኛ ክፍል ባልደረባችን ገብረ ገብረ መድህን የኢሮብ አድኮቬሲ ማህበር ሊቀመንበርንና የአካባቢውን ነዋሪዎችን በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅቷል፡፡

___________

ቪኦኤ በስልክ ያነጋገራቸው የኢሮብ ኣድቮከሲ ማሕበር ሊቀመንበር አቶ ስዩም ዮሃንስ ፣ “የኤርትራወታደሮች በኢሮብ ወረዳግድያና ፆታዊ ጥቃት ፈፅመዋል፣ ንብረት ዘርፈዋል፣ መኖሪያ ቤቶችንም ኣቃጥለዋል፡፡” ይላሉ፡፡ በተለይም ከታህሳስ 28 እና 29, 2013 ባሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ወታደሮቹ አድረሰዋል ያሉትን ጥፋት እንደሚከተለው ይገልጹታል

“በአባሎቻችን ያረጋገጥነው በግድያው 63 ሰዎች እንደሞቱ ነው። ቁጥሩ እስከ 70 ሊደርስ እንደሚችል ግን እንገምታለን። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ከተወሰዱ በኋላ ከሁለት ሶስት ሳምንታት ወይን ከእንድ ወር በኋላ ነው እሚነገረው፣ ወይም አስክሬናቸው የሚገኘው።”

አቶ ስዮም በኢሮብ ባህል፣ ስለ ፆታ መደፈር በግልጽ መናገር ከባድ በመሆኑ፣ በቁጥር ለመግለፅ ቢከብድም ወንጀሉ ስለመፈፀሙ ግን እርግጠኞች ነን ይላሉ፡፡

መውኻንና ሓረዞ በተባሉ ቀበሌዎች፣ የሚሊሻ ቤቶች ናቸው በሚል ሰበብ 58 ቤቶች በኤርትራ ወታደሮች መቃጠላቸውንም ሌሎች ወንጀሎች መፈጸማቸውንም ከስፍራው በደረሳቸው ሪፖርት ማረጋገጣቸውን አቶ ስዩም ተናግረዋል።

ተፈጽሟል ስላሉት ግድያና ሌሎች የሰብአዊ መብት በደሎች የክልሉን ጊዚያዊ አስተዳዳሪና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋን በአካል አግኝተው የነገሯቸው መሆኑንም አቶ ስዩም ይናገራሉ፡፡

“የክልሉን የጊዚያዊ አስተዳዳሪ ዶክተር ሙሉ በአካል አግኝቻቸው አንስቼባቸዋለሁ፡፡ ስለ ጉዳዩ በጣም ነው እሚሰማቸው። በጣም ነው እሚያዝኑት። ሃዘናቸውንም ገልፀውልኛል።ሁኔታውን ስገመግመው ግን ከሳቸው አቅም በላይ ነው።”

ግድያና ቃጠሎ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ዓሌተና፣ እና እንዳሞሳን ጨምሮ የተለያዩ ቀበሌዎች መሆናቸውን፣ ከተገደሉትም መካከል የእድሜ ባለፀጋዎዎች እንደሚገኙባቸው ገልጸው፣ በብዛት ወጣት ወንዶችና እንዲሁም የተወሰኑ ሴቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ፣ በሚኖሩበት የምስራቅ ትግራይ ዞን ወረዳ፣ ሳዕስዕ ፃዕዳ እምባ ቀበሌ ኮማሱ ብሓ፣ ልዩ ስሙ ውታፋ በተባለ ቦታ፣ የካቲት 16 2013 ዓ\ም ላይ ስድስት ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች የተረሸኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ በተለይ ከሁመራ ተፈናቅለው የመጡና ዓዲግራት ላይ የተፈናቃዮች እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩ ቆይተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መንገድ ላይ መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪው በሰጡት ምስክርነት ውታፋ በተባለ አንድ መንደር ውስጥ ብቻ የታጣቂ ሚሊሻ ቤቶች ናቸው በሚል ሰበብበኤርትራ ወታደሮች ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸውን የስምንት የገበሬዎች ስም ዘርዝረዋል።ታህታይ ዝባን በተባለ ቦታም እንዲሁ የ13 ገበሬዎች ቤት ጨምሮ “የወንድሞቼ፣ የቤተሰቦቼና የጎረቤቶቼ ቤቶች በሙሉ ተቃጥለዋል፤” ብለዋል፡፡

የስጋ ዘመዶቹና አብሮ አደግ ጓደኞቹ የተገደሉበት መሆኑን የተናገረው ሌላው ወጣት ምሁር ደግሞ በምእራብ ትግራይ፣ ወረዳ ታሕታይ ቆራሮ ማይ ጥምቀት በተባለ ቀበሌ፣ ሕዳር 8 2013 ዓ\ም ከ16 ዓመት ወጣት እስከ 80 ዓመት ኣዛውንት እሚደርሱ 30 ወንዶች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ተወልዶ ባደገበት አካባቢ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች በኗሪዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈፀሙ መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡

የኤርትራ ወታደሮች “በኢሮብ ግድያና ዝርፊያ ፈጽመዋል” ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:18 0:00

የአካባቢው ነዋሪ ወጣት እንደሚለው የኤርትራ ወታደሮች ያንን ሁሉ ግፍ ያደረሱት ውጊያ በሌለበት ምንም ዓይነት የትግራይ ሰራዊትም ሆነ ታጣቂ የሚሊሽያ ሃይል በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ።

“ዝም ብለው ብቻ በየቤቱ እየገቡና መንገድ ላይ ያዩትን ሰላማዊ ሰው ሁሉ ነው የገደሉት። በዛች ህዳር 8 2013 ዓ\ም እለት 30ሰዎችን ገድለዋል። ከነዚህ መካከል በወጉ የተቀበሩት ሶስቱ ብቻ ናቸው ። የተተቀሩት 27ቱን ግን በየተገደሉበት ቦታና ሜዳ ላይ ነው የተቀበሩት።”

ወጣቱ እንደሚለው የኤርትራ ሰራዊት በአካባቢው ሰፍሮ እንደሚገኝና ወደዚያ አካባቢ ሲመጡ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የሚሊሻዎችን ንብረት ናቸው በሚል የአካባቢውን ከብት ማይጕዕ ተብሃሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ውስጥ አጉረው መያዘቸውን ከ እነዚህም በጎችና ፍየሎችን እያረዱ የሚቀለቡ መሆናቸውንም ነዋሪው ተናግሯል፡፡

በምስራቅ ትግራይ ዞን ተፈፅመዋል ስለ ተባሉት ግድያዎችና ተቃጥለዋል ስለተባሉ ቤቶች የተጠየቁት የዞኑ ዋና ኣስተዳዳሪ ኣቶ ሃይለስላሴ ተስፋይ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል

“እኔ መረጃ ተሰብስቦ፣ ከተደራጀና ከተተነተነ በኋላ ነው እምሰጠው እንጂ ያልተደራጀና ያልተተነተነ መረጃ አልሰጥም።”

በሰሜን ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በታሕታይ ቆራሮ ወረዳ ቀበሌ ማይ ጥምቀት ተፈፅሟል ስለሚባለው የግዲያና ሌሎች ወንጀሎች መልስ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ይሁን እንጂ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ በቅርቡ በተለይ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ስላለው ውድመትና ጥቃት በአጠቃላይ ስላለው የጸጥታና የደህንነት ሁኔታ እንዲህ ብለዋል።

“የፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ብዙ ስራ ያስፈልገዋል። ገና እየጀመርን ነው ። እንደሚታወቀ ህዝባችን አይቶት እማያቀው ከባድ አደጋ ደርሶበታል። የንብረት ውድመት፣ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የወሲብ\ፆታዊ ጥቃት፣የተለያዩ ቀውሶች፣ በመሰረተ ልማት ሳይቀር ውድመት ደርሷል። በግጭቱ ወይም ጦርነቱ ብዙ ውድመት ደርሷል። ከግለሰቦች ንብረት ጀምሮ እስከ ትላልቅ የህዝብ ንብረትና ድርጅቶች ላይ በተለያዩ ሃይሎች ስርቆትና ውድመት ተፈፅሟል።”

የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ እንዲወጣ እየቀረበ ስላለው ጥሪም የተጠየቁት ዶክተር ሙሉ ነጋ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል

በነገራችን ላይ እዚህ ላይ ግልፅ አቋም ነው ያለው። የኤርትራ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም እዚህ ክልል ያለ ሃይል መውጣት አለበት። ይህን አካባቢ ሊቆጣጠረው የሚገባው ኃይል የመከላከያ ኃይል ነው። የሆነ ኃይል ካለ መውጣት አለበት። ምንም ጥርጥር የለውም። ጊዚያዊ አስተዳደሩ ክልሉን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ሃላፊነትና ስልጣን እንዲረጋገጥለት ነው እየታገልን እምንገኘው።

የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋ ስለተባሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚመረምር የገለጸ ሲሆን በክልሉ ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ተስትፈዋል መባሉን ግን የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥት አስተባብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG