በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ የሱዳን እርዳታ በቀይ ባህር እንዳይሄድ አገደ


ፎቶ ፋይል - የሱዳን ተፈናቃዮች በሱዳን የዳርፉር ክልል ኤል ፋሸር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዛም ዛም የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተሰብስበው
ፎቶ ፋይል - የሱዳን ተፈናቃዮች በሱዳን የዳርፉር ክልል ኤል ፋሸር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዛም ዛም የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተሰብስበው

መቀመጫቸውን በየመን ያደረጉት የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር መርከቦች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት፣ ከአስር ወራት በላይ በዘለቀው ጦርነት ለተጎዱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሰብአዊ ርዳታ ማቅረብ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና አስጊ እየሆነ መምጣቱን ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ አስታወቀ።

ድርጅቱ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ሱዳን የሚሄደው ርዳታ በቀይ ባህር ፋንታ፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሚገኘው ጀበል አሊ ወደብ በኩል እንደሚሆን አስታውቋል።

አዲሱ መስመር የትራንስፖርት ወጪን ከ40 በመቶ በላይ እንደሚያሳድገውም ገልጿል።

የተቋሙ ሠራተኛ ሳሉ አኛንጋ እንደገለፁት፣ አዲሱ መስመር ሁለት ሳምንት ከነበረው የማጓጓዣ ጊዜ ወደ አንድ ወር እንደሚጨምረውም አስረድተዋል።

"አማራጭ መንገዶቹ ረጅም ርቀት ያላቸው በመሆናቸው፣ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ርዳታዎች በጊዜው እንዳይደርሱ ያደርጋሉ" ያሉት አኛንጋ፣ ይህም ሥራችንን በጣም ፈታኝ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ አድርጎታል ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሚያዚያ 2023፣ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ታጣቂ ኃይሎች መካከል በተነሳው ጦርነት ምክንያት፣ ሱዳን ውስጥ ከ25 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የርዳታ ተቋማት አስታውቀዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የሰብአዊ ርዳታ ተቋማት፣ ባለሞያዎች እና አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ሁቲዎች በመርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት፣ መስመሩን ሸቀጦችን ለማስተላለፍ በሚጠቀሙበት አገሮች ደህንነት እና ኢኮኖሚ ላይ ስጋት ላይ እንደጣላቸው እየገለፁ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG