በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢራኑ ተቃውሞ ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጀኔራሉ አመኑ


ፎቶ ፋይል፦ አያቶላ አሊ ካሜኒ
ፎቶ ፋይል፦ አያቶላ አሊ ካሜኒ

በኢራን በመካሄድ ላይ በሚገኘው አገር አቀፍ ተቃውሞ እስካሁን ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አንድ የኢራን ጀኔራል ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ ማመናቸው ተነገረ፡፡

የኢራን አብዮታዊ ዘብ አየር ኃይል የህዋ ክፍል አዛዥ ጄኔራል አሚር አሊ ሃጂ ዛዴህ ቁጥሩን በይፋ የተናገሩት፣ ለጦሩ ቅርበት ባለው ድረገጽ ላይ መሆኑን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የሟቾቹ ቁጥር ሁለት ወር ባስቆጠረ ጊዜ ውስጥ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተሰማ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የተጠቀሰው ቁጥር ተቃውሞ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ሁኔታውን ኢራን ውስጥ በቅርበት ሲከታተል የቆየውና መሰረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ካስቀመጠው ግምት እጅግ የሚያንስ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ህዝባዊ አመጹ ከጀመረ አንስቶ እስካሁን 451 ተቃዋሚዎችና 60 የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ገልጾ ከ18ሺ ሰዎች በላይ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡

የተቃውሞው መነሻ ኢራን ውስጥ ከቤተሰቦችዋ ጋር ሳኬዝ ከተባለው ወደ ቴህራን ስትጓዝ በነበረችበት ወቅት ሂጃብን በትክክል አልተከናነብሽም በሚል እአአ መስከረም 13 በኢርሻድ አሳሾች የታሰረችው አሚኒ በፖሊሶች ቁጥጥር ስር እንዳለች በመሞቷ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG