በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የባህረ ሰላጤው አገሮች ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ


የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱላሂ፣ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቡ ዳቢ
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱላሂ፣ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቡ ዳቢ

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱላሂ በባህረ ሠላጤው አጎራባች አገሮች ያደረጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ፕሬዚዳንት ጋር በመወያየት አጠናቀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢራን መገለሏ እንዲቀንስላት እና ኢኮኖሚዋን ለማጠናከር በያዘችው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ኳታርን፣ ኩዌትን እና ኦማንን ከጎበኙ በኋላ ወደተባበሩት የአረብ ኢሚሬቶች መጓዛቸው ተነግሯል፡፡

ከተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በአቡ ዳቢ "የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ትብብርን ማጎልበት በሚቻልባቸው መንገዶች" መወያየታቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ኢራንን እንዲጎበኙ ከፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ የተላከውን ግብዣ ያቀረቡላቸው መሆኑንም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሀገሮቻቸው መካከል የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት እና የንግድና ቱሪዝም ዕድሎችን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውንም የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት በየመን እና ሶሪያ በተፈጠረው ግጭት የተነሳ ከኢራን ጋር እየተባባሰ የነበረውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG