የኢራኑ ከፍተኛ መንፈሳዊ መሪ፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዙሪያ ስለሚደረግ ድርድር ጉዳይ ማንሳታቸውን ተከትሎ በሰነዘሩት ትችት፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ የሚደረግ ድርድር “የብልሃት፣ አስተዋይነት የተመላ ወይም ክብር የሚቸረው ድርጊት አይደለም” ብለዋል።
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ፣ አያቶላህ አሊ ከሚኔ አክለውም፤ “እንደዚህ ካለ መንግስት ጋር ምንም አይነት ድርድር ሊኖር አይገባም" ብለዋል። ሆኖም ከዋሽንግተን ጋራ ንግግር እንዳይደረግ የሚል ትእዛዝ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከሚኒ ይህን ያሉት ዛሬ አርብ ቴህራን ላይ ለአየር ኃይል መኮንኖች ንግግር ባሰሙበት ወቅት ነው። አስተያየታቸው ቀደም ሲል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ የሚደረግን መሰል ድርድር በተመለከተ ይሁንታ ካሳዩበት አቀራረብ የሚቃረን ይመስላል። የ85 ዓመቱ ከሚኔ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የመደራደርን ሐሳብ በተመለከተ ሁሌም ጠንቃቃ ሐሳብ በመስጠት ይታወቃሉ።
ካሚኔ ይህን አስተያየት እንዲሰጡ የገፋፋቸው ምን እንደሆነ ለጊዜው ግልጽ አይደለም። ሆኖም፣ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ “ከፍተኛው ጫና” የሚሉትን አቀራረብ ዳግም ተግባራዊ የሚያደርግ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ቢፈርሙም ከቴህራን ጋራ ስለሚደረግ ግንኙነት ጠቁመው ነበር።
በጊዜው ከዋይት ሃውስ በሰጡት አስተያየትም ፕሬዝዳንታዊውን ትዕዛዝ "ልፈርም ነው። ሆኖም ብዙም አንጠቀምበት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
"ከኢራን ጋራ ስምምነት ማድረግ መቻል ያለመቻላችንን ግን እናያለን" ያሉት ትረምፕ “በኢራን ላይ ማጥበቅ አንፈልግም። ለነገሩ በማንም ላይ ቢሆን ማጥበቅ አንፈልግም። ሆኖም የኑክሌር ቦምብ ሊኖራቸው ግን አይችሉም” ሲሉ አክለዋል።
መድረክ / ፎረም