አንዲት ወጣት በፖሊሶች እጅ ባለፈው ሳምንት ህይወቷ ካለፈ በኋላ በመላ ኢራን የተቃውሞ ሠልፍ በመጠንከሩ፣ “የሃሰት ወሬና አሉባልታ የሚያሰራጩ ሰዎችን” ህግ አስፈፃሚው አካል ይክሰስ ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥሪ አድርጓል።
በመዲናዋ በቴህራንና በሌሎችም ከተሞች ተቃውሞው ምንም የመቀዝቀዝ ሁኔታ አላሰየም። የፖሊስ ጣቢያዎች በእሳት ሲጋዩ የፀጥታ ኃይሎችም ጥቃት ደርሶባቸዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ማሻ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ወጣት “ያልተገባ ልብስ” ለብሰሻል በሚል ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ከተያዘች በኋላ፣ በቁጥጥር ስር ባለችበት ወቅት ራሷን በመሳቷ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች። ባለሥልጣናት የሞቷን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተቃራኒው መንግሥትን የሚደግፍ ሠልፍ ለነገ ዓርብ እንደታቀደ ታውቋል።
በአሚኒ ሞት ምክንያት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ከእአአ 2019 ወዲህ በእስላማዊ ሪፖብሊኳ ትልቁ ነው ተብሏል። ኩርዶች በሚበዙበት ሰሜን ምዕራብ ኢራን ተቃውሞው የበረታ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ተቃውሞው 50 ወደሚሆኑ የሃገሪቱ ከተሞች ተዛምቷል ተብሏል።
ባሲጅ የተባለው ወታደራዊ መሰል የመንግሥት ደጋፊ ቡድን አንድ አባል በጩቤ ተወግቶ መገደሉን ሁለት የኢራን ዜና ወኪሎችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሚኒ ሞት፣ በሴቶች ላይ የተጣለውን አስገዳጅ አለባበስ የመሰሉ የግል ነፃነትን የሚጋፉ ጉዳዮች እንዲሁም በኢኮኖሚ ማዕቀብ ምክንያት ችግር ላይ የወደቀውን ኢኮኖሚ አስመልክቶ፣ በመንግሥት ላይ ያለውን ቁጣ እንደገና ቆስቁሶታል።