የጀርመን ባለሥልጣናት በኢራን አብዮታዊ ዘብ ላይ ሊጥሉ ያሰቡት ማዕቀብ ኃላፊነት የጎደለውና ገንቢም ያልሆነ ነው ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ለሪፖርተሮች ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደዚህ ያሉ ማዕቀቦች ህገወጥ ናቸው ብለዋል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ትናንት እሁድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጀርመንና የአውሮፓ ህብረት በኢራን አብዮታዊ ዘብ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እያሰቡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አብዮታዊ ዘቡን በአሸባሪ ድርጅትነት ዝርዝር ውስጥ እንዲመዘገብ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ እየታሰበበት መሆኑን ሚኒስትሯ ተናገረዋል፡፡
ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ሁሴን ሳላሚ ተቃዋሚዎች ካሁን ወዲያ የሚያካሂዱትን የተቃውሞ ሠልፍ እንዲያቆሙ ማስጠንቀቂያ በሰጡ ማግስት መሆኑ ተነግሯል፡፡
የእስልምናን ጥብቅ የአለባበስ ደንብ ጥሰሻል በሚል በሥነ ምግባር ፖሊሶች ቁጥጥር ስር እንዳለች ህይወቷ ያለፈውን የ22 ዓመቷ ማሃሳ አሚኒ ሞትን ተክትሎ ኢራን ውስጥ ለሳምንታት የተቃውሞ ሠልፍ ሲካሄዱ ሰንብቷል፡፡