እሥራኤል በሦሪያ ላይ ያደረሰችው የሮኬት ጥቃት አስቀድማ በፈጠረችው ምክንያት ላይ የተመሠረተ ነው ስትል ኢራን አስታወቀች።
የመንግሥቱ ዜና አገልግሎት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባህራም ጋሤሚን ጠቅሶ፣ ጥቃቱ የሦሪያን ብሄራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የጣሰ ነው ማለታቸውን ዘግቧል። ሦሪያም ወረራውን በመቃወም የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ነው ሲል አስረድቷል።
የእሥራኤል ጦር ሠራዊት፣ በአየር ኃይሎች ዒላማ የተደረጉትን በሦሪያ የሚገኙ የኢራን ጦር ሠፈሮች የሚያሳዩ ከአየር የተነሱ ፊልሞችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
‘The Jerusalem Post’ የተባለው የሀገሪቱ ጋዜጣም እሥራኤል ሃያ ሮኬቶች ከተተኮሱባት በኋላ በሦሪያ የሚገኙ ሃምሳ የኢራን ዒላማዎችን ደብድባለች ሲል ዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዪ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ አዲስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ፣ ግጭቶችና ትንኮሳዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።
የዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት በእሥራኤል ይዞታ ሥር በሚገኘው የጎላን ኮረብታ ኢራን አደረሰች ያለውን የሮኬት ጥቃት “ተቀባይነት የሌለውና እጅግ አደገኛ” ሲል አውግዟል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብም ለዚህ ግዴለሽ ጥቃት ሙሉ ኃላፊነት ይወስዳል ሲል አስጠንቅቋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ