ኢራን የኒውክሊየር መርሃ ግብሯን እንድትገታ የቀረቡላትን ዓለም አቀፍ ጥያቄዎች ወደ ጎን በመተው የዩሬኒየም ክምችቷን ለጦር መሣሪያ ማምረቻ ወደተቃረበ ደረጃ እያሳደገች ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሊየር ተቆጣጣሪ ተቋም ሚስጥራዊ ዘገባ አመለከተ፡፡
ትላንት ማክሰኞ አሶሲየትድ ፕሬስ ያገኘው የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ተቋም ዘገባ፣ ኢራን የዩሬኒየም ክምችቷን ወደ 60 ከመቶ ከፍ ማድረጓን አመልክቷል፡፡
ዘገባው እንዳመለከተው እ.ኤ.አ ጥቅምት 26 ኢራን 182.3 ኪሎ ግራም ዩሬኒየም ክምችት የነበራት ሲሆን በነሀሴ ወር ከወጣው ሪፖርት ወዲህ የ17.6 ኪሎ ግራም ጭማሪ አሳይቷል።
የዩራኒየም መጠኑ ክምችት 60 ከመቶ ደረሰ ማለት ወደ ሙሉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያነት ለመቀየር ያስፈልጋል ለተባለው የ90 ከመቶ መስፈርት ጥቂት የሚቀረው መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለጦር መሣሪያነት ሳይሆን ለልማት ዓላማ የሚውል መሆኑን ትናገራለች፡፡
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኅይል ቁጥጥር ተቋም ግን መርሃ ግብሩ በድብቅ ለጦር መሣሪያ ማምረቻ እንደማይውል ዋስትና እንደማይሰጥ አስጠንቅቋል።
ሪፖርቶቹ በቅርብ ወራት ውስጥ እስራኤል እና ኢራን በቅርቡ የሚሳይል ጥቃትን የተለዋወጡ ሲሆን ከአንድ አመት በላይ በዘለቀው የጋዛ ጦርነት እስራኤል እና በኢራን የሚደገፈው ሃማስ ውጊያ ወሳኝ ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ምንም እንኳ ኢራን ከዓለም ኃያላን ሀገራት ጋር የገባችው የኒውክሊየር ስምምነት እልባት ያላገኘ ቢሆንም የፕሬዝዳንት ትረምፕ ዳግም መመረጥ የተወሳሰበውን ጉዳይ በምን መልኩ ሊፈታው እንደሚችል ጥያቄ አስነስቷል፡፡
በዩናትይትድ ስቴትስ፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሣይ እና በጀርመን የሚመሩ ምዕራባውያን ሃገራት በቅርቡ በሚካሄደው የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኅይል ተቋም ቦርድ ስብሰባ ላይ ለስምምነቱ አለመሳካት ኢራንን ለመውቀስ አቅደዋል፡፡ ይህም ለተጨማሪ የኒውክሊየር መርሃ ግብሮች መባባስ ስጋት ሊሆን እንደሚችል አስግቷል፡፡
መድረክ / ፎረም