የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ፣ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ፣ ዛሬ ረቡዕ በኬንያ በመጀመር፣ ከፕሬዚዳንቱ ዊሊያም ሩቶ ጋራ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ከታቀደለት አንድ ቀን ዘግይቶ የጀመረው የፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ጉብኝት፣ በሦስት ሀገራት እንደሚደረግ ታውቋል። ራይሲ፣ ዩጋንዳንና ዚምባብዌን በዚኹ ሳምንት እንደሚጎበኙ ሲታወቅ፣ እስላማዊ ሪፐብሊኳ አገር፣ በዓለም የደረሰባትን መገለል ለመቀነስ በማለም፣ በዲፕሎማሲው መስክ ዐዲስ ኅብረት ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት አካል ነው፤ ተብሏል።
ጉብኝቱ፣ ከ11 ዓመታት በኋላ፣ በኢራን ፕሬዚዳንት ደረጃ የተደረገ የአፍሪካ ጉብኝት እንደኾነ ለትውስታ ተጠቅሷል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ የአፍሪካ አህጉር፥ የዲፕሎማሲያዊ ውጊያ መድረክ እንደኾነች የጠቀሰው የኤኤፍፒ ዘገባ፣ ሩሲያ፣ በዩክሬን ላይ ለፈጸመችው ወረራ፣ የአፍሪካውያንን ድጋፍ ስትሻ፣ የምዕራቡ ዓለምም ከአህጉሪቱ ጋራ ያለውን ግንኙነት ለማጥበቅ በመጣር ላይ ነው። ሕንድ እና ቻይና በበኩላቸው፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ወጪ መድበዋል፡፡
መድረክ / ፎረም