በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አይኦኤም ኢትዮጵያዊያንን ከየመን እየመለሰ ነው


ፎቶ - ፋይል
ፎቶ - ፋይል

አይኦኤም የመን ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሣቢያ በአደጋ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የጀመረውን ጥረት በመቀጠል በሁለተኛው ዙር በረራ ነገ እኩለ ቀን አካባቢ 275 ኢትዮጵያዊያንን እንደሚመልስ ተገልጿል፡፡

ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ከትናንት በስተያ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ በየመንና በሣዑዲ አረቢያ አዋሣኝ አካባቢዎች ላይ ከ1 ሺህ 900 በላይ ኢትዮጵያዊያን መንቀሣቀሻ አጥተው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት ሰሞኑን ባካሄደው የመመለሱ ሥራ የመጀመሪያ በረራ ከመካከላቸው 115ቱ ሕፃናትና ታዳጊዎች እንዲሁም 34ቱ ሴቶች የሆኑ ሁለት መቶ ሰባ አምስት ኢትዮጵያዊያንን ከየመኗ ሆዴይዳ አዲስ አበባ አድርሷል፡፡

አይኦኤም ጊዜያዊ ማቆያ አዲስ አበባ ላይ ያቋቋመ ሲሆን ከተመላሾቹ መካከል በጥይት የተመቱ፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍና ሌላም ሕክምና የሚያስፈልጋቸው አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

አይኦኤም ይህንን የመመለስ ሥራውን የጀመረው ባለፈው ኅዳር ቢሆንም የመን ውስጥ በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና የገንዘብም እጥረት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን፣ በኋላም እንቅስቃሴውን ቀጥሎ በቀጣዮቹ ሁለት ሣምንታትም ተጨማሪ ስድስት የመመለስ በረራዎችን እንደሚያደርግ አመልክቷል፡፡

ተመላሾቹ እየተመለሱ ያሉት በራሣቸው ጥያቄና በሙሉ ፍቃደኛነት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥትም ጥያቄ መሆኑን በፍልሰት ድርጅቱ የአዲስ አበባ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትና በሰዎች የመነገድ ወንጀል መከላከል ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ታገል ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡

የመን ውስጥ ችግር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ወደ ሣዑዲ አረቢያ ድንበር ለመዝለቅ በሚፈልጉበት ጊዜ የወሰን ችግሩ ጥብቅ በመሆኑ ሣቢያ የበረታ ችግር ላይ ይወድቃሉ ሲል የአይኦኤም ጋዜጣዊ ማስታወሻ አመልክቷል፡፡

አይኦኤም የሚያካሂደው ኢትዮጵያዊያኑን የመመለስ ተግባር እጅግ ውድ መሆኑን አቶ ታገል ጠቁመው እንደ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤትና የሕፃናት ፈንድ፣ እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሚያግዙት ገልፀዋል፡፡

የዘንድሮው የአውሮፓዊያኑ ዓመት ከገባ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 28 ሺህ 179 ኢትዮጵያዊያን ሕገወጥ በሆነ መንገድ የመን ውስጥ መግባታቸውን አይኦኤም አመልክቷል፡፡

ለአጠቃላዩ የሕገወጥ ሽግግርና የሰው ንግድ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመነጋገር በመጭው ወር አጋማሽ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ዓለምአቀፍ ስብሰባ እንደሚደረግና በሌላ በኩል ደግሞ ከባሕረ ሰላጤው ሃገሮች ትብብር ድርጅት ጋርም ምክክር ለማድረግ መታሰቡን የአይኦኤም ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታገል ሰሎሞን ገልፀዋል፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG