እሁድ መጋቢት 16/2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተመስገን ደሣለኝ ቤተሰቦች የጀሞ ኮንደሚኒየም መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው የምስጋና ዝግጅት ላይ ተይዘው ታስረው የነበሩት ዐሥራ አንድ ሰዎች ተለቀዋል።
በዕለቱ ተይዘው ታሥረው የነበሩት ዐሥራ አንድ ሰዎች እስክንደር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዘላላም ወርቃገኘሁ፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ማህሌት ፋንታሁና ይድነቃቸው አዲስ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ላይ አምደኖች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥም በጣም በቅርቡ ከእስር የተፈታውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ታስረው የተፈቱ ናቸው።
በተጨማሪም እንዲሁ በቅርቡ የተፈታው የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ አንዷለም አራጌን ጨምሮ ወይንሸት ሞላ፣አዲሱ ጌትነት፣ስንታየሁ ቸኮልና ተፈራ ተስፋዬም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜ ታስረው የተለቀቁ ናቸው።
እነ እስክንድር ነጋ ከመታሰራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ በባህርዳር ከተማ ታሥረው የነበሩ 19 የዩኒቨርስቲ መምሕራንና የአማራ ክልል ጋዜጠኞች በትናንትናው ዕለት መፈታታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ