በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ከግማሽ ቢልዮን ዶላር በላይ ለአፍሪካ ቀንድ ድርቅና ረሃብ ሰጥታለች


ዶ/ር ራጅ ሻህ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) አስተዳዳሪ
ዶ/ር ራጅ ሻህ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) አስተዳዳሪ

ቃለ ምልልስ ከዩኤስአይዲ አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር ራጅ ሻህ ጋር

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) አስተዳዳሪ ዶ/ር ራጅ ሻህ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለምልልስ ወደ አፍሪካ ቀንድ ተጉዘው የተመለከቱትን የበረታ ረሃብና የስደተኞች ሕይወት፣ በምላሹ ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስን ዝግጅትና ጣልቃ ገብነት፣ እንዲሁም የአካባቢው መንግሥታት ያላቸውን እርሣቸው “ቁልፍ” ያሉት ሚና አንስተው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ራጅ ሻህን ያወያያቸው ፍሬድ ኩፐር ነው፡፡

ኩፐር - ዶ/ር ሻህ፣ በቅርቡ የኬንያን የስደተኞች መጠለያ ሠፈሮች ከተመለከቱ በኋላ ያገኙትንና የሚሰማዎትን ይነግሩኛል?

ዶ/ር ሻህ - የመጠለያ ሠፈሮቹንና የአካባቢውንም ማኅበረሰብ ከተመለከትኩ በኋላ ያደረብኝ ስሜት የሰው ልጅ እንደምን የገዘፈና አሣዛኝ ፈተናዎችን እየተሸከመ እንዳለ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬ በሶማሊያና በአጠቃላይም በመላው አፍሪካ እየታየ ያለ ነው፡፡ እንደምናውቀው ይህ ድርቅ ባለፉት ስድሣ ዓመታት ውስጥ ያልታየና በምግብ እጦት ምክንያት 12 ሚሊየን ሰዎችን ለሥቃይ የዳረገ ነው፡፡

በዚያ ላይ እንዲት ሴት ጥቂት ኀዘኔታና ድጋፍ ለማግኘት ሰማንያ፣ መቶና መቶ አሥር ኪሎሜትሮችን በእግሯ የመጓዟን ነገር ስታየው የሁኔታው አሣዛኝነት የባሰ ይሆናል፡፡

ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ሠፈር ለመድረስ ልጀቻቸውን ለሰላሣ ቀናት ተሸክመው በእግራቸው የተጓዙ ሴቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ሁሉንም ነገራቸውን አጥተው ተንገላትተውና ተጎሣቁለው በመጨረሻ የተራቡ፣ በተቅማጥና በበሽታ የተሠቃዩ፣ ያለምግብና ያለውኃ ለብዙ ቀናት ቆይተው የደከሙ ልጀቻቸውን ብቻ ታቅፈው ቀርተዋል፡፡

በአራት ዓመት ዕድሜው 8 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ብቻ የሚመዝን ልጅ አይቻለሁ፡፡ መሠረታዊ ምግብ ሲሰጠው የነበረው በአፍንጫው በገባለት ማስተላለፊያ ነበር፡፡ እጅግ ለብዙ ቀናት ምግብ ባለመቅመሱ መብላት አይችልም ነበር፡፡ ጨርሶ ደክሟል፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉ በየዕለቱ ወደ ሠፈሮቹ የሚገቡ በሺሆችና በሺሆች የሚቆጠሩ ሰቶችና ሕፃናት አሉ፡፡ ከልክ ያለፈ እጅግ አሣዛኝ ታሪክ ነው፡፡

ኩፐር - ዩናይትድ ስቴትስና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እያቀረቡ ስላሉት እርዳታ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ዶ/ር ሻህ - ባለፈው ዓመት ዩናይትድ ስቴትስ የበረታ ረሃብ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በሚባለው አሠራር ምክንያት ሁኔታውን በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የበረታ ቸነፈር ወደአካባቢው እየመጣ እንደነበረ ከመስከረምና ከጥቅምት ጀምሮ ተንብየናል፡፡ በመሆኑም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እጅግ አጣዳፊ በሆነ የምግብ እጥረት ችግር ላይ እንዳይወድቁ ለመከለከል የምግብ እርዳታና ሌሎችም ድጋፎችን ወደአካባቢው ስናደርስ ቆይተናል፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ ለአምስት ሚሊየን ሕዝብ ከስድስት መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ የተደረገበት እርዳታ አድርሰናል፡፡ ከዚያ ውስጥ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ የዋለው 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰው በበረታ ችግር ላይ በሚገኙባት ሶማሊያ ውስጥ ለተከናወኑ የእርዳታ ሥራዎች ነው፡፡

ሌሎቹ የመርኃ ግብሩ ክፍሎች ከብቶችና ሌሎች እንስሣትን በመከተብ፣ ውኃ ለማኅበረሰቦች በማድረስ የግብርናውን ሁኔታ በምዕራብ ኬንያና በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች፣ በመሠረቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተባባሰ ረሃብ እንዳይጋለጡ በመሥራት ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ስለዚህ የነበረው ከፍተኛ የቁርጠኝነት ዝግጅትና ደረጃ ነበር፡፡ ሕይወቶችን ለማትረፍ ዓለም አሁን ይበልጥ መሥራት አለበት፡፡ በእኛ በኩል ግን ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡

ኩፐር - ስድስት መቶ ሚሊየን ዶላሩ በሙሉ የሚውለው ለድርቁና ለረሃቡ እርዳታ ነው?

ዶ/ር ሻህ - አዎን፡፡ በአንድ በኩል ለአጣዳፊ እርዳታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ሳይሰደዱ ባሉበት እንዲቆዩ ማኅበረሰቦችን ለማገዝ የዋለ ነው፡፡ ሌላው ከዚህ ሁኔታ የተማርነው ጉዳይ ሰዎች የሚፈልጉትን ምግብና ውኃ ያሉበት፣ የሚኖሩበት ቀዬ ካደረስክላቸው ምግብ፣ ውኃና ሕክምና ፍለጋ እንዲህ ዓይነት አደገኛና የተራዘሙ ጉዞዎችን ለማድረግ አይዳረጉም፡፡ ስለዚህ ሕይወቶችን ለማትረፍ ይህ የሚመረጠው መንገድ ነው፡፡ እስከአሁን ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ከብቶችን ከትበናል፡፡ ይህንን የምናደርገው እንዲህ ዓይነት ድርቅና ረሃብ በመጣ ጊዜ ከብቶች ስለሚታመሙና ስለሚያልቁ፣ በዚህም ምክንያት ቤተሰቦች መሠረታዊ የሆኑ ጥሪቶቻቸውን ስለሚያጡ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መንደሮቻቸውን እየጣሉ ለመሸሽ ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ሥራችን ምክንያት በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች በየአካባቢያቸውና በማኅበረሰቦቻቸው ውስጥ ሳይፈናቀሉና ሳይሰደዱ እንዲቀሩ ለማድረግ ችለናል፡፡

(ሙሉውን ቃለምልልስ ያዳምጡ)

XS
SM
MD
LG