በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከኢትዮጵያ አምልጦ የነበረው ‘ዋና ተፈላጊ’ ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪ ሱዳን ውስጥ ተይዟል - ኢንተርፖል


ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማሪያም
ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማሪያም

በዓለም “ዋና ተፈላጊው” ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪ ተብሎ ሲጠራ የነበረው ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማሪያም ሱዳን ውስጥ መያዙን ዓለም አቀፍ የፖሊሶች መረብ የሆነው ኢንተርፖል ትናንት ሐሙስ አስታውቋል።

የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ እንዳመለከተው ግለሰቡ የተያዘው በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተመራ አሰሳ ነው።

ከምሥራቅ አፍሪካ ተነስተው ሜድትሬኒያንን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ ፍልሰተኞችን በመጥለፍ፣ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ እንዲሁም በመግደል በሚሉ ወንጀሎች ኪዳኔ መከሰሱን በፈረንሳይ መሠረቱን ያደረገው ኢንተርፖል በመረጃ መረብ በለቀቀው መግለጫ አስታውቋል።

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማሪያም ኢትዮጵያ ውስጥ ተይዞ ፍርዱን በመከታተል ላይ ሳለ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከፍርድ ቤት ተሰውሮ እንደጠፋ ሪፖርቱ አስታውሷል።

በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተመራና በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖሊስ በተደረገ አሰሳ ግለሰቡ ሱዳን ውስጥ ባለፈው እሁድ ሊያዝ ችሏል ሲል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ግለሰቡ ሊያዝ የቻለው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መርማሪዎች የኪዳኔን ድርጅቶችና የቤተሰብ አባላት እንዲሁም ገንዘቡ የሚዘዋወርበትንና ወደ ሕጋዊነት የሚቀየርበትን ሂደት ተከታትለው ከደርሱበት በኋላ መሆኑ ታውቋል። ምርመራውም ወደ ሱዳን መርቷቸዋል ሲል ኢንተርፖል አስታውቋል።

ኪዳኔ “ቀዩ መጥሪያ” ተብሎ የሚጠራው የኢንተርፖል መጥሪያ ከኢትዮጵያና ከኔዘርላንድ እንደወጣበትና ሊቢያ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች የሚታጎሩበት ካምፕ ባለቤት ነው ሲል የኔዘርላንድ መንግስት በበኩሉ እንደከሰሰው የአሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርት አመልክቷል።

በሊቢያ የረጅም ግዜ መሪዋ ሞአመር ጋዳፊ በሃይል ከተወገዱ በኋላና አገሪቱ ትርምስ ውስጥ ስትገባ፣ ለሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሳይፍ ቢን ዛይድ አል ናህያን በትዊተር እንዳስታወቁት ዘጠኝ ወር በፈጀውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው አሰሳ የኔዘርላንድ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን መርማሪዎች ተሳትፈዋል።

XS
SM
MD
LG