በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በዩናይትድ ስቴትስ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ተገኝተዋል


አለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎቹ የዴሞክራሲ በጎ ፍቃደኞች ዳይሬክተር እንግሊዛዊው ጆን ኡልት እና ሄሪ ቡዝ በአሌክሳንድሪያ፤ ቨርጂኒያ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ (ስቲቭ ሄርማን/ቪኦኤ)
አለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎቹ የዴሞክራሲ በጎ ፍቃደኞች ዳይሬክተር እንግሊዛዊው ጆን ኡልት እና ሄሪ ቡዝ በአሌክሳንድሪያ፤ ቨርጂኒያ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ (ስቲቭ ሄርማን/ቪኦኤ)

ዛሬ፤ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም. ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘና በመጠናቀቅ ላይ ባለው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ታዛቢዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

አንዳንድ ግዛቶች በአለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ከተለያዩ ሃገራት የመጡ አለም አቀፍ ታዛቢዎችን አስተናግደዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በቨርጂኒያ ግዛት አሌክዛንድሪያ ከተማ ባለ የአካባቢው የስነ ጥበብ ማዕከል በተቋቋመ የምርጫ ጣቢያ ሁለት እንግሊዛዊያን ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ እንግሊዛዊያኑ በስፍራው የተገኙት ለመምረጥ አልነበረም፤ ምርጫውን ሊታዘቡ እንጂ።

የዴሞክራሲ በጎ ፍቃደኞች ዳይሬክተር የሆኑት ጆን ኡልት ለቅኝት በሚዘዋውሩባቸው ጣቢያዎች ሰዎች ምርጫ ለመታዘብ እንደመጡ ሲረዱ ግራ እንደሚጋቡ ይገልጻሉ። በዚህ የተነሳም ሁልጊዜም ቢሆን አስቀድመው መታወቂያቸውን እንደሚያሳዩም ይገልፃሉ።

ስለሁኔታው ሲያስረዱም “ሁሌም ቢሆን እራሳችን አስቀድመን ነው የምናስተዋውቀው። ብዙ ሰዎች በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ድንገት ሁለት እንግሊዛዊያን ሲከሰቱ ይገርማቸዋል።” ብለዋል።

በስፍራው የተገኙ የምርጫ ጣቢያው ሁለተኛ ኃላፊ አንድ ጥግ ላይ ቦታ ካስያዙዋቸው በኋላ ታዛቢዎቹ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ መራጮች ማንነታቸውን እያረጋገጡ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ድምጽ ሲሰጡ ይታዘባሉ። እነዚህ ታዛቢዎች መራጮቹ ምርጫ ለማድረግ ያልተገደበ ተደራሽነት ተመቻችቶላቸው ይሆን እንደሆነ ይቃኛሉ።

ይኸው በአሌክሳንድሪያ የሚገኘው የመራጮች ጣቢያ ወደ ውስጥ ዘልቀው መግባት ለማይችሉ ሰዎች መግቢያው ላይ ምርጫ የሚያደርጉበትን ሁኔታ አመቻችቷል።

የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው አብዛኞቹ መራጮችም አለም አቀፍ ታዛቢዎች በአካባቢው ምርጫ ስፍራው መገኘታቸው የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሮባቸዋል።

ኤድ ሳንቼዝ አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ጠበቃ ሲሆኑ “የዴሞክራሲ ጠበቃ የምትሰኘው አሜሪካ የምርጫ ታዛቢዎች ሲያሻት ትንሽ የሚያሳስብ ነው” ይላሉ። “ነገር ግን ደግሞ ታዛቢዎቹ ጭራሽ ከሚቀሩ መኖራቸውን እመርጣለሁ” ይላሉ።

ጡረታ የወጡት መምህርት ሎሪ ፋርንዎርዝም ታዲያ ሁኔታውን በተለየ መንገድ ነው የተረዱት።

“እንደሚመስለኝ ይሄ የዲሞክራሲ ቅርሳችን ነው። ምናልባትም በዴሞክራሲያችን እንድንኮራ ያበረታታን ይሆናል” ይላሉ።

የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው ሴድ ሜየርስ የተሰኙ የሰራዊት አባልም የመምህርት ሎሪን ሃሳብ ይጋራሉ። እነዚህ ታዛቢዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ዴሞክራሲ ሊማሩ ነው የመጡት ብለው ያስባሉ።

ኤድ ሜርየርስ “መምጣታቸው መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። በጉዳዩ ላይ ከላቁት መጥታቹ ተማሩ ነው የኔ አስተያየት” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

በምርጫ ጣቢያው የተገኘው ኤልራሺድ ኢብራሂም ትውልደ ሱዳናዊ ነው። ኤልራሺድ “በአለም ዴሞክራሲ ላይ ማማ ላይ የተቀመጥ ነን። እኛ ዓለምን ልንቆጣጠር እንጂ ዓለም እኛን ሊቆጣጠር አይገባም” ይላል።

ሱዳናዊው ስደተኛ ታዲያ ይህን ምርጫ በቀላሉ እንደምያየው ይናገራል። ለዚህ በምክንያት የሚያስቀምጠው ደግሞ የትውልድ ሃገሩ ሱዳን ዴሞክራሲን ለማስፈን በትግል ላይ መሆኗን ነው።

XS
SM
MD
LG