በመላው ዓለም የሚገኙ የመብት ተሟጋቾች እና ሠራተኞች፣ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን(ሜይ ዴይ) ዛሬ ሲያከብሩ፣ የደመወዝ ጭማሬን፣ የሥራ ሰዓት መቀነስንና የተሻሉ የሥራ ኹኔታዎች መፈጠርን የተመለከቱ ሌሎችንም ጥያቄዎች አንሥተዋል።
በኢንዶኔዥያ፣ በዓመታዊው የሜይ ዴይ ሰልፍ ላይ፣ በመዲናዋ ጃካርታ 50ሺሕ ሠራተኞች እንደሚሳተፉ፣ የሠራተኛ ማኅበራት አስታውቀዋል፡፡
ሠራተኞቹ፣ እንደ ዐዲስ የወጣው የሥራ ፈጠራ ሕግ እንዲሻር ጠይቀዋል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ፣ ዐዲሱን ሕግ ያወጡት፣ የውጪ መዋዕለ ንዋይ ወደ ኢንዶኔዥያ ለመሳብ በሚል ነው፡፡ የሕጉ ነቃፊዎች ግን፣ ሠራተኞችንና አካባቢን የሚጎዳ፣ ለባለሀብቶችም ያደላ ነው፤ ሲሉ ይተቹታል።
በፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ፣ ሠራተኞች ባካሔዱት ሠልፍ፣ መንግሥት፥ ዝቅተኛ የሥራ የክፍያ መጠንን እንዲያሳድግና የሥራ ዋስትና እንዲያስጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን - ሜይ ዴይ፣ በሰልፍ እና በሠራተኞች መብት ላይ በሚያተኩሩ ሌሎች ኹነቶች በበርካታ ሀገራት ይከበራል፡፡