በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ድብደባ በበረታባት የዩክሬኗ ሴቬሮዶኔትስክ ውጊያው ተጋግሏል


ፎቶ ፋይል፦ ሴቬሮዶኔትስክ ውስጥ በጦርነቱ የፈራረሰ የመኖሪያ ሕንፃ
ፎቶ ፋይል፦ ሴቬሮዶኔትስክ ውስጥ በጦርነቱ የፈራረሰ የመኖሪያ ሕንፃ

የሩሲያ ኃይሎች ምሥራቃዊ ዩክሬንን ለመቆጣጠር ግባቸው ቁልፍ በሆነችውና በከባድ መሣሪያ ድብደባ እያወደሟት በምትገኘው ሴቬሮዶኔትስክ የዩክሬን ኃይሎች በሚያደርጉት የሌት ተቀን የጎዳና ውጊያ ይዞታቸውን እንደያዙ መቆየታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ከሴቬሮዶኔትስክ ወንዝ ባሻገር የሚገኙት ሴቬሮዶኔትስክና መንታዋ ከተማ ሊሲቻንስክ በሉሃንስክ ግዛት የመጨረሻዎቹ የዩክሬን ኃይሎች ይዞታዎች ሲሆኑ ሩሲያ እንደ ዋነኛው ግቧ አድርጋ ልትቆጣጠረው የወሰነችው አካባቢ ነው።

የዩክሬን የደኅንነት ምክር ቤት ፀሀፊ ኦሌክሲ ዳኒሎቭ ትናንት፤ ሀሙስ በሰጡት መግለጫ ሴቬሮዶኔትስክ ላይ ያለው ሁኔታ “እጅግ በጣም የተወሳሰበ”ና “የሩሲያ ኃይሎች ያላቸውን ኃይል ሁሉ ያሰለፉበት” ከተማ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሩሲያዊኑ “ለሰዎቻቸው አይሳሱም። ወታደሮቻቸውን እያግተለተሉ የመድፍ እራት ያደርጓቸዋል። ጦራችንን ቀንና ሌሊት በከባድ መሣሪያ እየደበደቡ ነው” ብለዋል ዳኒሎቭ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል።

በትንሿ የኢንዱስትሪ ከተማ ያለውን ወጀብ ወደራሷ የበላይነት ለመቀየር ዩክሬን ግዙፉን የሩሲያ ኃይል መቋቋም የሚያስችሏት ተጨማሪ ከባድ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጓት ገልፃለች።

ስለጦርነቱ ከከተማው አልፎ አልፎ ከሚገኙ መረጃዎች የዩክሬን ብሄራዊ ክብር ዘብ “ስቮቦዳ” ክፍለ ጦር አዛዥ ፔትሮ ኩሲክ በሰጡት የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ “ዩክሬናውያኑ ሩሲያውያኑን ወደ ጎዳና ውጊያ ስበው በማስገባት የከባድ መሳሪያ የበላይነታቸውን አሳጥተዋቸዋል” ብለዋል።

አያይዘውም “ትናንት ለኛ በጣም የተሳካ ዕለት ነበር። መልሶ ማጥቃት የጀመርን ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲያውም አንድ ወይም ሁለት ሠፈሮች ያህል ወደ ኋላ ገፍተናቸዋል” በማለት ያለውን ሁኔታ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ሩሲያዊያኑ ለሚተኩሷቸው ከባድ መሳሪያዎች ምላሽ ለመስጠት ኃይላቸው “እጅግ በሚያሳዝንና አደገኛ በሆነ መልኩ የመሳሪያ እጥረት እንዳለባቸው” ገልፀው ተጨማሪ ድጋፍ ቢያገኙ “የውጊያውን ሜዳ ውጤት ሊለውጠው እንደሚችል” ተናግረዋል።

ሮይተርስ ስለ ጦር ሜዳው ውሎ የተሰጡ መረጃዎችን ማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል።

በስተደቡብ በኩል ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸውና ተጭና ማስተዳደር በምትፈልጋቸው በኼርሶንና ዛፖሪዥያ ክፍላተ ሃገር ባካሄዱት መልሶ ማጥቃት በከሄርሰን አዲስ ቦታ መቆጣጠራቸውን የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በምሽቱ መግለጫቸው “የወራሪዎቹን ዕቅድ በማሰናከል በኩል የተሳካ ሥራ እየሠራንባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል በዛፖሪዥያ ግዛት መጠነኛ ድል እየቀናን ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ ዝርዝር አልሰጡም።

ሮይተርስ በዛፖሪዥያ ወይም በኼርሶን ስላሉት ሁኔታዎች ከገለልተኛ ወገን አለማረጋገጡን አስታውቋል።

ወኪሎቿን በሁለቱም ክፍላተ ሃገር ያስቀመጠችው ሩሲያ ግዛቶቹ ከሩሲያ ጋር እንዲቀላቀሉ ውሣኔ-ህዝብ ለመጥራት ማቀዷን አስታውቃለች።

ሩሲያ “አካባቢውን ትጥቅ ለማስፈታትና ከናዚዎች ነፃ ለማድረግ” በሚል ባለፈው የካቲት 17 በጎረቤቷ ዩክሬን ላይ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” መጀመሯን ከገለፀችበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠር ህይወት ጠፍቷል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል፤ ተሰድደዋል።

በሞስኮ 350ኛውን የሩሲያውን ዛር (ንጉሥ) የታላቁ ጴጥሮስን (ፕዮትር)ን የልደት በዓል ለማክበር በተደረገ ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ባሰሙት ንግግር “የሩሲያ ምድር” ብለው የጠሩትን “በድል አድራጊነት የማስመለስ ታሪካዊ ኃላፊነት” ያለባቸው መሆኑን ካሁኑ ሁኔታ ጋር አገናኝተዋል።

“ታላቁ ፕዮትር ታላቁን የሰሜን ጦርነት ለ21 ዓመታት ተዋግቷል። በርግጥ ከስዊድን ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረና ከነሱ አንድ ነገር የወሰደባቸው ይመስላል። አስመለሰ እንጂ (የሩሲያ የነበረነውን) ከነሱ ምንም ነገር አልወሰደም” ብለዋል ፑቲን በንግግራቸው።

የሴቬሮዶኔትስክ ከንቲባ ኦሌክሳንደር ስትርዩክ እስካሁን ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የከተማው ነዋሪ ቁጥራቸው ወደ አሥር ሺህ የሚጠጉ ሰዎች (በግምት አንድ አሥረኛ የሚሆኑ) እዚያው ከተማው ውስጥ ተቆርጠው መቅረታቸውን ተናግረዋል።

ሩሲያዊያኑ ከሴቬሮዶኔትስክ በስተምዕራብ ባለው ሉሃንስክና አጎራባቿን ዶኔትስክን በሚያካትተው ዶንባስ ክልል ያሉትን ዩክሬናዊያን ከበባ ውስጥ ለመክተት ከሰሜንና ከደቡብ እየገፉ መሆናቸው ተዘግቧል።

ዛሬ ሀሙስ ሩሲያ ዶኔትስክና ሉሃንስክ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ 20 ከተሞችን በመደብደብ 49 ቤቶችን አውድመዋል ወይም ጉዳት አድርሰዋል፤ በርካታ ፋብሪካዎችን፣ የባቡር ጣቢያዎችን ማወደማቸውንና ሁለት ሲቪሎች መገደላቸውን የዩክሬን ጦር አስታውቋል።

ሩሲያ ሲቪሎችን ዒላማ እንደማታደርግ ትናገራለች።

XS
SM
MD
LG