ዛሬ ማክሰኞ በተካሄደውና እየተጠቃለለ ባለው አጋማሽ ምርጫ፣ የአሜሪካ መራጮችን ድምፅ እንዲሰጡ ከገፏፏቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የዋጋ ግሽበት እና የፅንስ ማቋረጥ ዋናዎቹ ናቸው።
ወንጀል፣ ፍልሰት እና የጠመንጃ ፖሊሲ ተከታይ ጉዳዮች መሆናቸውን ኤዲሰን የተሰኘ ጥናት አጥኚ ተቋም ከድምፅ ሰጪዎች የሰበሰበው አስተያየት አመለከተ።
የመራጮች ተሳትፎ የተወካዮች ምክር ቤቱ በማን አብላጫ መቀመጫ ቁጥር ሥር ሆኖ እንደሚቀጥል እና የክልል እንደራሴዎችን ቁጥር የሚወስን ሲሆን እኩል ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ወንዶች መሳተፋቸውን የተሰበሰበው አስተያየት አመልክቷል።
ከድምፅ ሰጪዎች የተሰበሰበው የዳሰሳ ጥናት አጠቃላይ ግኝቶች የሚከተሉት ናቸው
• ከ10 መራጮች መካከል ስድስቱ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሮዪ እና ዌድ በመባል የሚጠራውን ሕግ በመሻር ባሳለፈው ውሳኔ አለመደሰታቸውን ወይም መናደዳቸውን የገለፁ ሲሆን ተመሳሳይ መቶኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ፅንስ ማስወረድ ሕጋዊ መሆን አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
• ከ10 መራጮች መካከል ሦስቱ እንዴት እንደሚመርጡ ለመወሰን የዋጋ ንረቱ በዋናነት የሚያሳስባቸው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
• ከ10 መራጮች መካከል ሦስቱ የፅንስ ማስወረድ ጉዳይ ለምርጫ ውሳኔያቸው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናገዋል።
• ከ10 መራጮች አንዱ ወንጀል እንዴት እንደሚመርጡ ለመወሰን በዋናነት የሚያሳስባቸው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል
• ከ10 መራጮች አንዱ የፍልሰት ጉዳይ የምርጫ ሁኔታቸውን ለመወሰን አሳሳቢ እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
• ከ10 መራጮች አንዱ የጠመንጃ ፖሊሲ እንዴት እንደሚመርጡ ለመወሰን በዋናነት የሚያሳስባቸው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል
• ከ10 መራጮች መካከል ስምንት የሚሆኑት ኢኮኖሚው "በጣም ጥሩም በጣም መጥፎም አይደለም" ያሉ ሲሆን ከ10 መራጮች ሁለቱ "በጣም ጥሩ ወይም ጥሩ" ነው ብለዋል።
• ከ10 መራጮች ስድስቱ በቅርብ ግዜ የቤንዚን ዋጋ ለገንዘብ ችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል
• ከ10 መራጮች መካከል ስድስቱ ፅንስ ማስወረድ ህጋዊ መሆን አለበት ያሉ ሲሆን ከ10 መራጮች አራት የሚሆኑት ደግሞ ህገወጥ መሆን አለበት ብለዋል
• ከአስር መራጮች አምስቱ የቤተሰባቸው የፋይናንስ ሁኔታ ከሁለት አመት በፊት ከነበረው የከፋ እንደሆነ ሲናገሩ ከ10 መራጮች 3ቱ አልተለወጠም፣ 2ቱ ደግሞ የተሻለ ነው ብለዋል
• ከ10 መራጮች ሰባቱ የአሜሪካ ዲሞክራሲ ስጋት ላይ ወድቋል ብለዋል
• ከ10 መራጮች ሰባቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሁለተኛ ግዜ ሲወዳደሩ ማየት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል
• ከ10 መራጮች ስድስቱ ለትራምፕ ጥሩ ያልሆነ አስተያየት ሲኖራቸው፣ ከ10 መራጮች 4ቱ ደግሞ ጥሩ አስተያየት አላቸው።
• ከመራጮች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የባይደንን የትምህርት እዳ ስረዛ ሲቀበሉት ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው መራጮች ደግሞ አይቀበሉትም