የተራውን ሕዝብ ስሜት አቀንቃኝ የመሰሉ ፖለቲከኞች በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለማቋረጥ የሚደርሷቸው ጥቃቶች ዋና በሚባሉ ዲሞክራሲያዊ ሃገሮች ውስጥ ሥጋት እየጋረጡ መሆናቸውን ሁለት ዓለምቀፍ የነፃ ፕሬስ ተሟጋቾች ዛሬ አስታውቋል።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድንና ፍሪደም ሃውስ ዛሬ ይፋ ባደረጉት ዓመታዊ የፕሬስ ነፃነት ሪፖርት ሚዲያውን በማጉደፍ ጋዜጠኞችን በመዝለፍና ዕገዳዎችን እናደርጋለን የሚሉ ማስፈራሪያዎች ተጠቅመዋል ሲሉ ምዕራባውያን መሪዎችን በሰላ ሂስ ጠርበዋል።
ፍሪደም ሃውስ በሪፖርቱ፣ ከ5 ዓመታት በፊት በሚዲያው ላይ የሚደርሱ ዓለምቀፍ ተፅዕኖዎች በዩናይትድ ስቴትስና በአውሮፓ ዲሞክራሲያዊ ሃገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አያደርሱም ነበር። ዛሬ ግን በነዚህ ሃገሮች ውስጥ በሕዝብ የተወደዱ የሚመስላቸው መሪዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ላይ ከባድ ስጋት ደቅነዋል ብሏል።
ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በበኩሉ በዲሚክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች፣ ሚዲያውን የሚመለከቱት የዲሞክራሲ ዋና አካል አድርገው ሳይሆን እንደ ተቃዋሚ መሆኑ በጣም ያሳስባል ሲል አስጠንቅቋል።
በእነዚህ ሁለት ዓለምቀፍ የነፃ ፕሬስ ተሟጋች ድርጅቶች ይበልጥ የተነቀፉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ናቸው።
ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን “ሚዲያውን የመስደብ አባዜ የተጠናወታቸው” ሲላቸው ፍሪደም ሃውስ በበኩሉ ትረምፕ ሚዲያውን እንደ አሜሪካ ሕዝብ ጠላት አድርገው ማቅረባቸው በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል ሲል አስጠንቅቋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ