በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሕንድ በጎርፍ ለተጠቃችው ኬንያ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ላከች


ወጣቶቹ ከባዱ ዝናብ በጎዳናዎች ላይ የፈጠረውን ወንዝ ሲያቋርጡ ናይሮቢ ማትሃሬ አካባቢ፣ እአአ ግንቦት 8/2024
ወጣቶቹ ከባዱ ዝናብ በጎዳናዎች ላይ የፈጠረውን ወንዝ ሲያቋርጡ ናይሮቢ ማትሃሬ አካባቢ፣ እአአ ግንቦት 8/2024

ሕንድ በዛሬው እለት በኬንያ በደረሰው አደገኛ ጎርፍ በተጥለቀለው አካባቢ የሚኖሩ ተጎጅዎችን ለመርዳት የሚውል ሁለተኛ ዙር የሰብአዊ እርዳታ መላኳን አስታወቀች።

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር ቀድሞ ቲውተር ይባል በነበረው እና አሁን ኤክስ በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አገራቸው የኬንያን ሕዝብ ለመርዳት በዛሬው እለት የላከችው እርዳታ 40 ቶን የሚመዝን የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒቶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል። ሕንድ ከኬንያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሚያጠናክረው በዚህ እርምጃዋ ባለፈው አርብ ግንቦት 2, 2016 ዓም የተለያዩ የምግብ እና የረድኤት ቁሳቁሶች ያሉበትን እርዳታ መላኳም ታውቋል።

በምስራቅ አፍሪቃ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ በሚነገርላት ኬንያ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የወረደው ከባድ ዝናም ባስከተለው አደገኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 228 ሲደርስ፤ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው ተዘግቧል።

የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለው ዝናም በያዝነው የግንቦት ወርም ተባብሶ እንደሚቀጥልም ተተንብይዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG