በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሞዲ እና ትራምፕ ውይይት በንግድ፣ ስልታዊ ግንኙነት እና በስደት ዙሪያ ያተኩራል


የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ
የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ዛሬ ሐሙስ በዋይት ሃውስ ያነጋግራሉ፡፡

የኒው ደልሂ ባለስልጣናት የሞዲ ጉብኝት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ አዲስ እና ተጨባጭ የኾነ አጋርነትን እንደሚያበስር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ሆኖም ተንታኞች ትራምፕ ቀዳሚ በሚያደርጓቸው እንደ ንግድ እና ኢሚግሬሽን ጉዳዮችን በተመለከተ አከራካሪ ነጥቦች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

ሞዲ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከፕሬዝደንቱ ጋራ እንደሚገናኙ ቀደም ብሎ የተነገረ ሲሆን፤ የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚሪ ህንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው” ብለዋል፡፡ “ዩናይትድ ስቴትስ ከጠንካራዎቹ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን አንዷ ናት” ሲሉም አክለዋል፡፡

የዋይት ሀውስ የብሔራዊ ምጣኔ ሃብት ምክር ቤት ዳይሬክተር ኬቨን ሃሴት ሰኞ እለት ከሲኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ህንድ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚገድብ ታሪፍ አላት" በማለት ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኒው ደልሂ በእሷ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት ለማርገብ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከአሜሪካ የሚገቡ ቅንጡ መኪኖች እና ሞተር ቢስኪሌቶች ላይ የታሪፍ ቅነሳ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡

ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ በብረታ ብረት እና በአሉሚኒየም ምርቶች ላይ የጣሉት የቅርብ ጊዜ 25 በመቶ ታሪፍ በህንድ ላይ ብቻ የተወሰነ ተጽዕኖ ቢኖረውም፤ ህንድ እስካሁን የትራምፕ ታሪፍ ተጽዕኖ አልደረሰባትም፡፡

የህንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ለዚህ ምክንያቱ ኒው ዴሊ ለአሜሪካ መጠኑ አነስ ያለ ብረታ ብረት ላኪ ሀገር መሆኗ ነው፡፡ በአንጻሩ ህንድ ከዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያዎች እና የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን ትገዛለች፡፡ በቅርቡ ፕሬዝዳንት ትረምፕ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጋራ ባደርጉት የስልክ ጥሪ ህንድ የግዢ መጠኗን ከፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የስደተኞች ጉዳይ ሁለቱ ሀገራት የሚያተኩሩበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ህንድ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ዜጎቿን ለመቀበል ትብብር ብታሳይም፤ 104 የሚሆኑ ህንዳውያን ከ40 ሰዓት በላይ በሰንሰለት ታስረው መላካቸው፤ በተለይም በህንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ቁጣ አስነስቷል፡፡

የህንድ ባልሥልጣናት ኒው ደልሂ የተሻለ የስደተኞች አያያዝ እንዲኖር ትጠይቃለች ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ህንድ በዋናነት ለትምሀርት እና ለስራ የሚመጡ ህንዳውያንን እና ኤች ዋን ቢ (H1B) ቪዛም በተመለከተ ለመወያየት አቅዳለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG