በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የነፃነት ቀን - ውቢት አሜሪካ


የዩናይትድ ስቴትስ ልደት
የዩናይትድ ስቴትስ ልደት

የነፃነት አዋጅ ከተነገረበት ከሰኔ 29/1768 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ልክ 243 ዓመት ሆነ። ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ነፃ መንግሥት ዕድሜ ነው።

የነፃነት ቀን - ውቢት አሜሪካ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:17 0:00

ልክ የዛሬ 243 ዓመት የዚህ ዘመናዊ ዴሞክራሲ ፈጣሪ አባቶች የነፃነት አዋጅ መቱና ከታላቋ ብሪታንያ አገዛዝ እንግዲህ ነፃ መሆናቸውን ለሎንዶንም፣ ለዓለምም ነገሩ።

በርግጥ ይህቺ ወጣት ሃገር ባለፉ ወደ ሁለት ተኩል ምዕት ዓመት በሚጠጉ ዓመታቷ ከነጣ ድኅነትና ከለየለት ጦርነት እስከ ዓለም የዘመኑ ሥልጣኔና የካብት ቁንጮነት እጅግ የበዙ ፈተናዎችን፣ መከራዎችን፣ ድሎችና ስኬቶችን አሣልፋለች።

ዛሬ ልጆቿ “ውቢት አሜሪካ” እያሉ ይዘምሩላታል። ዓለም ይፈልስባታል፤ ተስፋ ይፈስስባታል።

ፎርዝ ኦቭ ጁላይ (በሃገሬው አጠራር) ወይም ሰኔ 27 በኢትዮጵያው አቆጣጠር ሲውል አሜሪካዊያን ዘር፣ ቀለም፣ ኃይማኖት፣ የፖለቲካ ወገን፣ የኑሮ ደረጃ፣ ዕድሜና ፆታ፣ ሌላውም ለዓለም ልዩነት ሁሉ ምክንያት የሆነ እንከንና ዝባዝንኬ ሳይሸነቁጣቸው በአንድ ልቦናና ቀልብ እንደ አንድ ሰውና እንደ አንድ አሜሪካዊ በሃሴት ያከብሩታል።

የዘድሮው የነፃነት ቀን አከባበር ከወትሮው ለየት ያሉ ዝግጅቶች ታስበውበታልና በሰዉም መካከል የሃሣብ መለያየት የተፈጠረ ይመስላል።

በዚህ ዕለት ፕሬዚዳንት ተናግሮ አያውቅም፤ እንዲያው ከሕዝቡና ከቤተሰቡ ጋር ዋይት ሃውስ ውስጥ ሆኖ ያከብረዋል እንጂ። 45ኛው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ግን ያንን ባሕል ሊለውጡት ወስነዋል። ዛሬ በግዙፉ ብሄራዊ አደባባይ /ናሽናል ሞል - ተብሎ ይጠራል/ እንደወትሮው ለሚገጠገጠው አሜሪካዊና ከየትም ለሚሰባሰበው ሃገር ጎብኚ ሁሉ እዚያው እሰዉ መካከል ተገኝተው ከሊንከን መታሰቢያ ሃውልት ደጃፍ ንግግር ሊያደርጉ ነው።

በዚህ ዕለት ወታደራዊ ሠልፍ ተደርጎ አያውቅም፤ እንዲያው ሠራዊቱ በየግንባሩም፤ በየሠፈረበት ሁሉም በያለበት ሆኖ ከሕዝቡ ጋር ሕዝብ ሆኖ ያከብረዋል እንጂ። የዛሬው ፎርዝ ኦቭ ጁላይ ግን ወታደራዊ ትዕይንቶችም ሊደረጉበት ነው። ምንም እንኳ የጦር ኃይሎቹ ጠቅላይ አዛዥ ባለፈው ዓመት ፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላይ ተገኝተው በብሄራዊ ቀኗ “ባስቲይ ዴይ” ሻምዝ ኤሊዜ ጎዳና ላይ ያለፈውን ትንግርት የተባለ ወታደራዊ ሠልፍ ካዩ በኋላ እጅግ በመመሰጣቸው የጦሯቸውን ሞገስና ኃያልነት ለድፍን ዓለም የሚናገር የአደባባይ ትዕይንት ለማድረግ አስበው የነበረ ቢሆንም ይወጣል የተባለው ካዝናቸውን በእጅጉ የሚፈታተን ሆኖ ተገኘና ተዉት። ትተው ግን አልተውትም። ዛሬ የዋሺንግተን ዲሲ ጎዳናዎች በታንኮችና በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ይናጣሉ ተብሏል። የዋና ከተማዪቱ ሰማዮች ከጦር ግንባር በቀር ውለው የማያውቁ ጄቶች ይሽሞነሞኑባቸዋል ተብሏል።

ለማንኛውም በተለይ እነዚህ ሁለት አዳዲስ ክንዋኔዎች ሰዉንም ፖለቲከኛውንም ለሁለት ከፍለዋል።

“ታላቁ ዴሞክራሲያችን፣ ለሃገር ፍቅር የሚደረግ ታላቅ ጥሪ... ይላሉ የፕሬዚዳንት ትረምፕ ልዩ አማካሪ ኬሊያን ኮንዌይ - የዚህ አስተዳደር ስኬት፣ ለሰዎቻችን የፈጠርናቸው የሥራ ዕድሎች .. ለአርበኞቻችን ያደረግነው ሁሉ።” --- ኮንዌይ የዕለቱን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መከበር አስፈላጊነት ተናግረዋል።

በተወካዮች ምክር ቤቱ የዋሺንግተን ዲሲ እንደራሴ ኤሊኖር ሆልምስ ይህንን የዛሬውን አከባበር “በሙሉው ቀን ላይ የተዘረጋ ዶናልድ ትረምፕን ለማሞካሸት የተሰናዳ ፓርቲ የለየ፣ የፖለቲካ ትርዒት ነው” ብለውታል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይህንን ዕለት ለእራሱ የፖለቲካ ጥቅም ሲያውለው የአሁኑ በታሪክ የመጀመሪያ ነው” ይላሉ።

አንዳንዶቹ “ክብር ለጦር ሠራዊታችን ይሁን” እያሉ ትርዒቱን በጉጉት ይጠብቃሉ። ሌሎች ደግሞ “እርግጥ ክብር ለጦራችን ይሁን” ማለትን ባይዘነጉም ዕለቱ የጦር ትርዒት ሳይሆን የነፃነትና የደስታ የአሜሪካ ሕልም የሚጎላበት ነው ይላሉ። አንዳንዶች ዕለቱ የማንም የፖለቲካ መልዕክት ማስተላለፊያ ሳይሆን የአሜሪካዊያን ሁሉ ነውና ፕሬዚዳንቱ እዚያ አደባባይ ቆመው የእንደገና ምረጡኝ ቅስቀሳ አካል ተደርጎ የተቆጠረ ንግግር ማድረግ የለባቸውም ሲሉ ሌሎች ደግሞ “የለም፤ ፕሬዚዳንት እኮ ነው። ያሻውን ማድረግ ይችላል፤ ደግሞም እስኪ እንስማቸው” ይላሉ።

ለማንኛውም ዛሬ ከተለየ ፕሬዚዳንት ጋር የተለየ ፎርዝ ኦቭ ጁላይ፤ የተለየ የነፃነት ቀን ነው - ለአሜሪካ። የዛሬ ርችቷም ከወትሮው ውብና ድንቅ የሆነ፤ በየዓመቱ በጉጉት ከሚጠበቅ የሃያ ደቂቃ ትዕይንት ወደ ሰላሣ አምስት ደቂቃ ከፍ እንደሚል ማስታወቂያ ተነግሯል።

የግሩቺ ርችቶች አቅራቢ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፊል ግሩቺ ብሄራዊው አደባባይ ላይ ዝግጁ “አሜሪካ እንዲህ ናት” ይላሉ። “ታላቅ ነገርን ማድረግ እንሻለን - ትንግርት ይሆናል---“

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG