በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፕሬዚዳንት ጆሴፍ አር ባይደን በዓለ ሲመት


ጆሴፍ አር ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ
ጆሴፍ አር ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ ሥልጣን ሽግግር፣ በትናንትናው እለት፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዷል፡፡

ለየት ያለ የጸጥታ ጥበቃ በተካሄደበት ሁኔታ፣ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አር ባይደን፣ ትናንት ረቡዕ፣ በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተካሄደው በዓለ ሲመት፣ የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላቸውን ፈጸመዋል፡፡

ባይደን አስተዳደራቸው ቅድሚያ የሚሰጥባቸው አጣዳፊ ጉዳዮችንም ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ሥልጣናቸውን ከተቀዳጁበት ከትናንትናው እለት ጀምሮ አንዳንድ ውሳኔዎችንም ከወዲሁ መውሰድ ጀምረዋል፡፡

የ78 ዓመት እድሜ ባለጸጋና ዴሞክራቱ ባይደን፣ ለ36 ዓመታት ሴነተር እና የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ አሁን የ46ኛው የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ጆሴፍ አር ባይደን በዓለ ሲመት
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:11 0:00

የሰላምና ህዝባዊ አንድነት ጥሪ

ባይደን ቃለ መሃላቸውን ሲፈጽሙ፣ ቆሙውበት የነበረው ቦታ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ወረው፣ የአመጽ ጥቃት የፈጸሙበት ቦታ ነበር፡፡

ባይደን ጥቃቱን ለሰነዘሩና የምርጫውን ውጤት ለመቀልበስ ለሚተጉ ሰዎች የማያወላዳ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ እንዲህ አሉ

“ዴሞክራሲ ተሰባሪ ናት፡፡ በዚህች ሰዐት ግን ወዳጆቼ! ዴሞክራሲ አብባለች፡፡”

“የሁላችሁም ፕሬዚዳንት ነኝ” ያሉት ባይደን ፣ አሜሪካውያን አንድ ሆነው በህብረት ወደፊት እንዲራመዱም ጥሪያቸውን እንዲህ በማለት አሰምተዋል

“ፖለቲካ እኮ በመንገዱ ያገኘነውን ነገር ሁሉ መደመሰስ የለበትም፡፡ ሁሉም አለመግባባት ጭልጥ ወዳለው ጦርነት መክተት አይኖርበትም፡፡ እውነታዎች ራሳቸው የሚጠመዘዙበትና በሀሰት የሚፈረኩበትን ልማድና ባህል ማወሰገድ አለብን፡፡”

ፈተናዎች

ባይደን የፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ዘርፈ ብዙ ቀውሶችን እንሚያስተናግድ ጠብቀዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 400ሺ አሜሪካውያንን የገደለው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ አንዱ ነው፡፡

“ቫይረሱ እጅግ በበረታበትና አደገኛ በሆነበት ሁኔታና ጊዜ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ፖለቲካችንን ወደ ጎን አድርገን አንድ አገር በመሆን ይህን ቫይረስ ለመጨረሻ ጊዜ ልንፋለመው ይገባል፡፡” ብለዋል ባይደን፡፡

ባይደን የምክትል ፕሬዚዳነቷን ከማላ ኻሪስንም ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

ከማላ ኻሪስ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የምክትል ፕሬዚድትነቱን ሥልጣን ሲይዙ የመጀመሪያዋ ሴት፣ የመጀመሪያዪቱ ጥቁር እና የህንድ ዝርያ ያላቸው አሜሪካዊት ናቸው፡፡

በተለምዶ ይደረጉ የነበሩና፣ በዓለ ሲመቱን የሚያደምቁ የጎዳና ላይ ዝግጅቶች፣ በጸጥታው ችግር እና በኮረና ቫይረስ ወረርሽኙ ምክንያት ዘንድሮ አልተደረጉም፡፡

የሥነ ሥርዓቱን ጸጥታ ለማስከበር ታይቶ በማይታወቅ መጠን፣ 25 ሺ የሚሆኑ የብሄራዊ ዘብ ወታደሮች በከተከማዪቱ ፈሰዋል፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችም ተገድበዋል፡፡

በአሜሪካ የ150 ዓመት ፕሬዘዳንታዊው ታሪክ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በበዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ያልፈቀዱት የቀድሞ ፕሬዚድንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡

ትራምፕ አሸናፊውንና እሳቸውንም የሚተካውን ሰው እንኳን ደስ አለዎት አላሉም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ግን ፕሬዚዳንቱን ተክተው ልማዱን ፈጸመዋል፡፡

ይህን ያስተዋሉት ፕሬዚዳንት ባይደን ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል

“እኔነቴንና የልቤን ማንነት ተረዱ፡፡ እንዲህም ሆኖ ካልተግባባን ይሁን፡፡ ዴሞክራሲ ማለት እሱ ነው፡፡ አሜሪካ ማለት እሱ ናት፡፡ ሰላማዊና ጨዋነት በተመላበት መንገድ የመቃወም መብት!”

ባይደን የፕሬዚዳንትነቱ ሥልጣን የጨበጡት አጋሮቻቸው የዴሞክራ ፓርቲ አባላት ሁለቱንም ምክር ቤቶች በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ሊፈጽሙ ለሚፈልጓቸው አጀንዳዎችና ፖሊሲዎች ቀና መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡

ከአጀንዳዎቻቸው መካከል በተለይም እንደ የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ፣ የስደተኞችን ጉዳይ ማሻሻልና በውጭው ዓለም የአሜሪካንን ገጽታ መልሶ መገንባት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ባይደን ስለዚሁ ሲገልጹ እንዲህ አሉ

“አጋርነታችንን አድሰን ከዓለም ጋር ዳግም እንገናኛለን፡፡ ይህንንም ስናደርግ የትናንቶቹን ፈተናዎች ሳይሆን የዛሬዎቹንና የነገዎቹን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ነው፡፡”

የተላለፉ ውሳኔዎች

ባይደን ቃለመሃላቸውን ከፈጸሙ ሰዐታት በኋላ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፣የአስፈጻሚ ትዕዛዛትን አውጥተዋል፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቀልብሰውት የነበረውን፣ የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደገና መመለስን ጨምሮ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ተቋርጦ የነበረውን የሥራ ግንኙነት መመለስ የሚያስችለውን ውሳኔዎች አሳልፈዋል፡፡

ከተወሰኑ የሙስሊም አገሮች የሚመጡ ዜጎችን የሚያግደውን የትራምፕ የአስፈጻሚ ትዕዛዝንም ሽረዋል፡፡

በአሜሪካ ታሪክ፣ የ78ቱ ዓመት ባይደንን ያህል፣ የዕድሜ ጸጋ ይዞ፣ ፕሬዚዳንትነቱን የጀመረ አዛውንት የለም፡፡

ይሁን እንጂ ባይደን፣ የአስተዳደር አጀንዳዎቻቸውን በ10 ቀናት ውስጥ አስወንጨፈው ለማስነሳት ተነስተዋል፡፡

የአሜሪካን ኢኮኖሚ እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ እና ለኮረና ቫይረስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ድጋፍ ማግኘት፣ በዋነኞቹ እቅዶቻቸው የሚካተቱ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንታዊውን የሥራ አሰፈጻሚነት ሥልጣናቸውን በመጠቀም፣ የኮረና ቫይረስን በሚመለከት፣ በዛሬው እለት ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ ቀናት፣ የሥልጣን ዘመናቸው ውስጥ፣ 100 ሚሊዮን የሚደርሱ ክትባቶች እንዲሰጡ፣ ቀደም ሲል ያሳወቁትን እቅድ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

“ይህ ትልቅ አገር እኮ ነው፡፡ እኛም ጥሩ ሰዎች ነን” ያሉት ባይደን በአገራችን የገጠሙንን ፈተናዎች፣ የተስፋፋውን በሽታ፣ ጥላቻ፣ አመጽ፣ መለያየት እና ተስፋ ማጣትን ሁሉ በዴሞክራሲና በህዝባዊ አንድነት መወጣትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

(ከተለያዩ የአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢዎች የተጠናቀረ)

XS
SM
MD
LG