በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለባይደን ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ጥበቃው ተጠናክሯል


ፎቶ ፋይል፦ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
ፎቶ ፋይል፦ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

በሚቀጥለው ሳምንት እኤአ ጥር 20 የሚደረገውን የተመራጩን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት አስመልክቶ፣ ህግ አስከባሪዎችና በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ ያሉ ባለሥልጣናት፣ የጸጥታ ጥበቃውን ከወዲሁ ለማጠናከር እስከ ዛሬ ታይቶ የማይታወቅ የደህንነት እምርጃዎችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡

ይህ መሆኑ ባለፈው ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች፣ በምክር ቤቱ ህንጻ የፈጸሙት ሁከት እንዳይደገም በማሰብ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የዛሬ ሳምንት ረቡዕ፣ እኤአ ጥር 20/2021፣ የሚካሄደውን የተመራጩን ፕሬዘዳንት፣ ጆ ባይደን በዓለ ሲመት፣ ባለፈው ሳምንት ከታየው ዓይነት ሁከት ለመጠበቅ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የህግ አስከባሪ አካላት፣ ከወዲሁ በተጠንቀቅ ተዘጋጅተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች፣ ደም ያፋሰሰ አመጽ ማካሄዳቸው ይታወቃል፡፡

ከተለያዩ ክፍለ ግዛቶች የተወጣጡ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የብሄራዊ ዘብ አባላት፣ ከዚህ ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ፣ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ መግባት ይጀምራሉ፡፡

የዋሽንግተ ዲሲ ከንቲባ ሙረዬል ባውዘር፣ "የባይደን በዓለ ሲመት ፣ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንስቶ፣ እስከ ጽንፈኞች ማስፈራሪያ ድረስ ያልተጠበቁ አደጋዎችን ደቅኗል" ብለዋል፡፡ እንዲህ ብለዋል ባውዘር

“ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚመጡት ሰዎች ባላፈው ጊዜ የምክር ቤቱን ህንጻ ሲወሩ ካየናቸው ሰዎች የተለዩ ናቸው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ወደዚያ ምክር ቤት በመግባት ያንን ወረራ ያካሄዱ ሰዎች የተደራጁና ሥልጠናም እንዳላቸው ያሳዩ ይመስሉኛል፡፡”

የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍ.ቢ.አይ፣ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ፣ በ100ሺዎች የሚቆጠሩ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ምስሎች፣ በጥቆማ መልክ የደረሱት መሆኑን ገልጾ፣ 160 በሚሆኑት ላይ፣ የምርመራ ፋይሎች መከፈቱን አስታውቋል፡፡

በዋሽንግተን የኤፍ.ቢ.አይ የመስክ ምርመራ ረዳት ድሬክተር ስቲቨን ደአንቱኦኖ እንዲህ ብለዋል

“ትኩረት ያደረግነው በአመጽ ክሶች ላይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን ወሳኝ እንደሆኑት ዓለም አቀፍ የሽብርና የጸረ ሽብር ጸጥታ ጉዳዮች አድርገን ነው የምንመለከታቸው፡፡”

በሚችገን ዩኒቨርስቲ የጸረ ሽብር ባለሙያ የሆኑት ሰይድ ጃቬድ “የውጭ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ይልቅ፣ የአገር ውስጥ ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ የራሱ የሆነ የተወሳሰቡ የህግ ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡” ይላሉ፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ

“እዚህ አገር ጉዳዩን የምትመለከተው፣ አሜሪካ ውስጥ ተወልዶ ካደገ፣ በህገ መንግስቱ ብዙ ከለላዎችና ጥበቃዎች የሚደረግለትን ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እነሱም ይህንን ያውቁታል፡፡ ድርጊቱን ከመፈጸማቸው በፊት፣ መብታቸው እስከ የት እንደሚወስዳቸውና በወንጀል የሚያስጠይቃቸው ወሰን የቱጋ ተጀምሮ የቱጋ እንደሚያልቅ ያውቁታል፡፡” ብለዋል፡፡

ጆ ባይደን፣ በዚህ ሳምነት መጀመሪያ ላይ፣ ከአሜሪካ ድምጽ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በዓለ ሲመት ላይ፣ በልማድ እንደሚደረገው፣ እሳቸውም ቃለ መሃላቸውን በውጭ ሆነው ለመውሰድ እንደማይፈሩ ተናግረዋል፡፡

“እኔ አደርጋለሁ፡፡ ቢሆንም ግን እነዚያ የአመጽ አደጋን የሚደቅኑ ሰዎች፣ የሰዎችን ህይወት ለማጥፋት የሚዝቱ ሰዎች፣ የህዝብን ንብረት ያወድሙና ትልቅ ጥፋት የፈጸሙት ሰዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡”

ባለፈው ሳምነት በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ የተካሄደውን ጥቃት፣ የቀኝ ክንፍ ጽንፈኞችና የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች፣ በድረ ገጾች ላይ ሲቀሰቅሱ እንደነበር፣ ባለሥልጣናት ለሳምንታት ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ ትኩረታቸውን ፣ በፕሬዚዳንታዊው በዓለ ሲመት ላይ ሊያደረጉት ባሰቡት ተጨማሪ ጥቃቶች ላይ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡( ዘጋባው የቪኦኤ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳስክዋራ ነው፡፡)

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

ለባይደን ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ጥበቃው ተጠናክሯል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:22 0:00


XS
SM
MD
LG