በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ከኤርትራ መንግሥት ተያያዥ አካላት ላይ ማዕቀብ ጣለች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ዩናይትድ ስቴትስ በስድስት ከኤርትራ መንግሥት እና ከገዢው ፓርቲ ጋር በተያያዙ አካላት ላይ ማዕቀብ መደንገጓን አስታወቀች።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ ማዕቀቦቹ የተደነገጉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው መስከረም ወር በፈረሙት አስፈጻሚ ትዕዛዝ መሰረት መሆኑን አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ የኤርትራ ኃይሎች ኢትዮጵያ መገኘት፣ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ በማደርግ እና ግጭቱን በማራዘም ውጊያው እንዳያከትም ትልቅ ዕንቅፋት ደቅኗል ብለዋል።

የኤርትራ ኃይሎች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ ሪፖርቶች አሉ ያሉት ሚኒስትር ብሊንከን አስከትለውም በግጭቱ የሚሳተፉት ሁሉም ወገኖች የሚፈጸሙት አድራጎት ዩናይትድ ስቴትስን አብዝተው ማሳሰባቸውን ቀጥለዋል ብለዋል። የኤርትራ ኃይሎች በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አስከትለውም የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የያዙትን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደግፋለን ብለው የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ዕድሉን ተጠቅመው ካለ ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ያለ አንዳች ገደብ የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነት እንዲፈቅዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የዛሬው ማዕቀብ ዒላማ ያደረገው በኤርትራ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ላይ ቢሆንም በግጭቱ የሚሳተፉት ወገኖች፣ የሁሉም ባህሪ አሁንም አብዝቶ እያሳሰበን ነው ያሉት ሚኒስትር ብሊንከን ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ተያያዥ በሆኑ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማእቀብ አሁን ያልደነገግነው ውይይቶቹ ውጤት ያመጡ እንደሆን ለማየት ጊዜ ለመስጠት በማሰብ ነው ብለዋል። ሆኖም ወገኖቹ ትርጉም ያለው እርምጃ የማያሳዩ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ነጻ እውጭ ግንባርንም የሚያካትቱ ተጨማሪ ማዕቀቦች ለመደንገግ ዩናይትድ ስቴትስ ዝግጁ ነች ብለዋል።

እነዚህ ማዕቀቦች ቀውሶቹን እንዲቀጥሉ በሚያደርጉ ላይ እንጂ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ወይም በአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ላይ ያነጣጠሩ አይደሉም ሲሉም አክለው አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG