የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይኤምኤፍ) ባለሥልጣናት፣ ለኢትዮጵያ ሊያደርጉት ስለአቀዱት ድጋፍ ቴክኒካዊ ሥራን ለማከናወን በአገሪቱ እንደሚገኙ፣ ሮይተርስ የዜና ወኪል የተቋሙን ቃል አቀባይ ጠቅሶ ዘግቧል።
የገንዘብ ተቋሙ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ የድጋፍ ጥያቄ እንደደረሰው ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፥ በድርቅ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በአገር ውስጥ ግጭት እንዲሁም፣ ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ወረራ መፈጸሟ በአስከተለው ዳፋ ምክንያት አገሪቱ ብዙ ችግር አይታለች፤ ብለዋል።
“አንዱ ፕሮግራም የሚያተኩረው፣ በአገሪቱ ባለሥልጣናት የቀረበውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመደገፍ፥ የኢኮኖሚ፣ የሰብአዊ እና የማኅበራዊ ችግሮቿን ለመቅረፍ እንዲሁም፣ ሥራን በመፍጠር እና ድህነትን በመቀነስ ኢኮኖሚዋን እንድታረጋጋ ለማገዝ ነው፤” ሲሉ የተቋሙ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
በዚህ ሳምንት እየተካሔደ ያለው ቴክኒካዊ ውይይት፣ በገንዘብ ተቋሙ እና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል፣ ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ተከታይ መኾኑንና የሰብአዊ እና የኢኮኖሚ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በተሻለ ለመቅረፍ ያለመ እንደኾነ ቃል አቀባይዋ ጠቁመዋል።
ዜናውን በቅድሚያ ያበሠረው፣ ብሉምበርግ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ የገንዘብ ተቋሙ ባለሥልጣናት፣ ለ10 ቀናት በኢትዮጵያ እንደሚቆዩ ይጠበቃል።
አይኤምኤፍ፣ ዘላቂ ሰላምንና መረጋጋትን ለማምጣት የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና ከዚያም በኋላ በኢትዮጵያ የታየውን መሻሻል በመልካም እንደሚያየውና ተግባራዊነቱም በመልካም ኹኔታ እየሔደ እንደኾነ እምነቱን ገልጾ፣ በትግራይ ክልል የሰብአዊ እና የመሠረታዊ ግልጋሎቶች መመለስንም በበጎ እንደሚመለከተው ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ የጠየቀችው የዕዳ ቅነሳ ፕሮግራም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ምክንያት ተስተጓጉሎ ነበር። የአይኤምኤፍ ዋና የገንዘብ ምንጭ የኾነችው አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት እና ተባባሪ ኀይሎች ሠቆቃዎች ተፈጽሟል፤ የሚል ነቀፌታ ከአሰማች በኋላ፣ ከአገሪቱ ጋራ ያላትን ግንኙነት ለማንበር እየሠራች መኾኑን ሪፖርቱ ጨምሮ ጠቁሟል።