በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ኢኮኖሚ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት እንደተዳከመ ተነገረ


የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂቫ
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂቫ

የኮቪድ-19 ክትባት መዳረስን በተመለከተ በባለጸጋዎቹ እና እጅግ ደሃ በሆኑት ሃገሮች መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት የአለም ኢኮኖሚን ማገገም ያጓትተዋል ሲሉ የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ።

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂቫ ትናንት ማክሰኞ ጣሊያን ውስጥ በበይነ መረብ አማካይነት በተካሄደ ጉባዔ ላይ ባሰሙት ንግግራቸው አይኤምኤፍ በመጭው የዓለም ኢኮኖሚ ትንበያው የዘንድሮ እአአ 2021ን የኢኮኖሚ ትንበያ ዝቅ እንደሚያደርገው አስታወቀዋል።

የዚህም ምክንያቱ በይበልጥ ተላላፊ የሆነው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሳቢያ የበሽታ ስርጭት ከፍ ማለቱ እና በበርካታ ሃገሮች ያለባቸው የእዳ ጫና እና የዋጋ ንረት እየተባባሰ መምጣቱ መሆኑን አስረድተዋል።

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ ባለፈው ሃምሌ ባወጣው ትንበያ የዓለም ኢኮኖሚ በስድስት ከመቶ እንደሚያድግ ተንብዮ የነበረ ሲሆን ዋና ሥራ እስኪያጇ ሲናገሩ ኢኮኖሚው አሁንም በኮቪድ-19 እና ተያያዥ ጉዳቶች የተነሳ ገና እየተንገዳገደ ነው ብለዋል።

ባለጸጎቹ ሃገሮች በገቡት ቃል መሰረት ለታዳጊ ሃገሮች የኮቪድ ክትባቶቹን ካልሰጡ በስተቀር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የአምስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርሳል ሲሉ አሳስበዋል። ከክትባቱ ሌላ ታዳጊ ሃገሮች ለምርመራ ለንክኪ ክትትል ሥራ እና ለመድሃኒት የሚያስፈልጋቸውን ሃያ ቢሊዮን ዶላር ባለጸጎቹ ሃገሮች ማሟላት አለባቸው ብለዋል።

አይ ምኤፍ ይህ የአውሮፓ አቆጣጠር 2021 ከማብቃቱ አስቀድሞ በሁሉም ሃገሮች ቢያንስ አርባ ከመቶው እስከ መጪው 2022 አጋማሽ ደግሞ ሰባ ከመቶው መከተብ አለበት ብሎ የያዘው ዕቅድ አሁንም ቢሆን መሳካት የሚችል ነው ብለዋል የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተሯ ክሪስታሊና ጂዮርጂቫ።

XS
SM
MD
LG