የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ እንደሚገኝ፣ አንድ ከፍተኛ የገንዘብ ሚኒስቴር ባልሥጣንን በመጥቀስ ሮይተርስ ዘግቧል።
ለዋና አበዳሪዎቿ ክፍያ የመፈጸሚያው ግዜ የደረሰባት ኢትዮጵያ፣ ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሟ የሚውል 3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከገንዘብ ድርጅቱ ጋራ በመነጋገር ላይ መሆኗን ጉዳዩን የሚያውቁ ሦስት ምንጮቹን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የብድር ጥያቄን በተመለከተ ለመነጋገር አንድ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ፣ የገንዘብ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ ባለፈው ወር አስታውቀው ነበር። አይኤምኤፍ አንድ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ እንደሚገኝ ማረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል።
“ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ድጋፍ ማድረን በተለመለከተ ከመንግስት ጋራ ገንቢ ውይይት ለማድረግ የአይኤምኤፍ ልዑክ በአገሪቱ ይገኛል” ሲሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የብድር ክፍያዋን በተመለከተ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ እፎይታ እንዲኖራት ያቀረበችው ጥያቄ፣ እስከያዝነው የፈረንጆች ወር መጨርሻ ድረስ ከአይኤምኤፍ ብድር የማታገኝ ከሆነ ተቀባይነት አያገኝም ሲል የፓሪስ ክለብ በመባል የሚታወቀው የአበዳሪ አገራት ቡድን ባለፈው ታህሳስ አስጠንቅቆ ነበር።
ኢትዮጵያ ባለፈው ታህሳስ ለዩሮ ቦንድ መክፈል የነበረባትን 1ቢሊዮን ዶላር መፈጸም ባለመቻሏ፣ በአፍሪካ ዕዳዋን መክፈል ያልቻለች ሶስተኛ አገር ሆና ተመዝግባለች፡፡
መድረክ / ፎረም