በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢጋድ በኢትዮጵያ እና በኦሮሞ ታጣቂ ቡድን መካከል የቀጣይ ድርድር ተስፋውን ገለጸ


ፎቶ ፋይል፦ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ
ፎቶ ፋይል፦ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት(ኢጋድ)፣ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የተደረገው ድርድር ያለስምምነት ቢጠናቀቅም፣ ወደፊት ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚኖሩ ተስፋ እንዳለው አስታውቋል።

በኢጋድ እና በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ፣ በፌዴራሉ መንግሥት እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚንቀሳቀሰው ዐማፂ ቡድን መካከል፣ በታንዛኒያ - ዳሬ ሰላም ከተማ የተካሔደው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ያለውጤት ተጠናቋል።

ላለፉት አምስት ዓመታት የተካሔደውን ደም አፋሳሽ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ ለማስቆም በሚል፣ ለኹለተኛ ጊዜ የተካሔደው የታንዛኒያ ድርድር እንዳይሳካ ዕንቅፋት በመፍጠር፣ ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ ተካሰዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ሲባል፣ ሁለቱም ወገኖች ለሰላሙ ሒደት ያሳዩትን ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ”

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ሲባል፣ ሁለቱም ወገኖች ለሰላሙ ሒደት ያሳዩትን ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ” መማፀናቸውን የጠቀሰው የኢጋድ መግለጫ፤ ዶክተር ወርቅነህ፣ ሁለቱም ወገኖች ችግሮችን ለመፍታት ዐዲስ ዙር ንግግሮችን ይጀምራሉ፤ የሚል ተስፋ እንዳላቸው አመልክቷል።

“ኢጋድ በኹኔታው ላይ መሥራቱን ይቀጥላል፤ ሁለቱም ወገኖች፣ ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቅረፍ ለሚያደርጉት ጥረት የማያቋርጥ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነው፤” ብሏል መግለጫው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተወካዮች፣ የመጀመሪያ ዙር ንግግራቸውን፣ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት፣ ታንዛኒያ ላይ አድርገው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ በቅርቡ ለተደረጉት ድርድሮች አለመሰካት፣ የታጣቂውን ቡድን “ግትርነት” እና “የማይጨበጡ ፍላጎቶች” ተጠያቂ አድርገዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ፍላጎት የለውም፤ ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት “የአሸባሪ ድርጅት” ብሎ የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ እ.አ.አ በ2018፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦነግ) የትጥቅ ትግል ማቆሙን በማስታወቁ ከቡድኑ ከተነጠለ ወዲህ፣ ከመንግሥት ጋራ ሲፋለም ቆይቷል። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ፣ የዐማፂው ቡድን ዓላማ ተጋሪ ነን፤ የሚሉ፣ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችም የተነሡ ሲኾን፣ አብዛኞቹ የላላ መዋቅር ያላቸው ናቸው።

እ.አ.አ በ2018፣ በጥቂት ሺሕዎች የሚገመቱ አባላት የነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ ቢመጣም፣ አንዳንድ ታዛቢዎች፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠር የሚችል የፖለቲካ ኀይል በሚኾንበት ደረጃ አልታጠቀም፤ ብለው ያምናሉ።

ሰራዊቱ፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን በማካሔድ በዐቢይ መንግሥት ክስ የሚቀርብበት ሲኾን፣ ዐማፂ ቡድኑ ግን ክሱን ያስተባብላል። መንግሥትም፣ ቡድኑን ለማጥቃት በሚል በሕዝብ ላይ ኢ-ፍትሐዊ የጅምላ ርምጃዎችን በመውሰድ ክስ ይቀርብበታል፡፡ ይህም በአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ቅሬታንና ቁጣን ፈጥሯል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG