ባለፈው ሚያዝያ ወር የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከኮረም፣ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች፣ ወደ ዋግ ኽምራ እና የሰሜን ወሎ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች፣ ያለበቂ ሰብአዊ ድጋፍ ለሦስት ወራት መቆየታቸውን ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ ጎዳና ላይ ከመተኛት ጀምሮ ለልመና መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
በአኹኑ ወቅር እርሳቸውም ተፈናቃይ መኾናቸውን የገለጹት እና ኮረም ከተማን ለሁለት ዓመት በከንቲባነት የመሩት አቶ ብርሃኑ ኀይሉም፣ ከሦስቱ ወረዳዎች የተፈናቀለው ሕዝብ ብዛት ከ22ሺሕ እንደሚልቅ ጠቅሰው፣ የምግብ አቅርቦቱ እጥረት አሳሳቢ መኾኑን አመልክተዋል፡፡
በርካታ ተፈናቃዮችን እንደተቀበለ የተገለጸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ ዞኑ ካለበት የሀብት ውስንነት ባሻገር፣ በአካባቢው ድርቅ በመከሠቱ ለተፈናቃዮቹ ሕይወት አድን ድጋፍ ለመስጠት መቸገሩን አስታውቋል፡፡
የዐማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣ ለተፈናቃዮቹ የምግብ አቅርቦት ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥ አረጋግጧል፡፡
መድረክ / ፎረም