በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ለትግራይ የመድሃኒት አቅርቦት ማድረሱን አስታወቀ


ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ካለፈው መስከረም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግራይ መቀሌ የመድሃኒት አቅርቦት ማድረስ መቻሉን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

በባላሥልጣናት ድጋፍና ትብብር መሰረታዊ መድሃኒቶችና በአስቸኳይ ተፈላጊ የሆኑ የክህምና አቅርቦቶች ዛሬ ረቡዕ መቀሌ መድረሳቸውንና በክልሉ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰራጩ መሆናቸውን የኮሚቴው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የጤና አስተባባሪ አፖሎ ባራሳ "የመጀመሪያው የመድሃኒት አቅርቦት ሆስፒታል መድረሱ ትልቅ እፎይታ ነው" ብለዋል፡፡

አያይዘውም "እነዚህ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የህይወት አድን እርዳታዎች ናቸው፣ የእነዚህ እርዳታዎች መቀጠል ምን ያህል ወሳኝ መሆናቸውን ለመግለጽ ይቸግረኛል" ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ቀይመስቀል በመጭዎቹ ቀናትና ሳምንታት የህክምና እርዳታ አቅርቦቶችን ለመላክ ማሰቡንም አመልክቷል፡፡

የጸጥታው ሁኔታው ከፈቀደም ሰብአዊ እርዳታዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በየብስ ለመላክ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም የቀይ መስቀል በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙና በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማትም እርዳታዎቹን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

"አስተባባሪዋ ባራሳ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ሠራተኞች አስቸኳይ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ምላሽ ለመስጠት እጅግ በጣም አሰቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሠሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች እርዳታው በጣም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ ሁኔታዎችን እንድሚያመቻቹም መጠየቃቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG