በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረስ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት በቀጠለበት እና በከበባ ውስጥ በምትገኘው ጋዛ ሰብዓዊ ቀውሱ እየጨመረ በሄደበት ወቅት፣ የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ የሚካሂዱትን ጥቃት አስፍተው ቀጥለዋል።
የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከባድ የቦምብ ፍንዳታ እና የአየር ላይ ጥቃቶች መፈፀማቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በደቡባዊ የጋዛ ክፍል በሚገኙ ካሃን፣ ዩኒስ አንድ ራፋም የአየር ጥቃት መፈፀሙን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የእስራኤል ጦር በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኙት አል-ቡሬጅ እና በዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎች በፍጥነት ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሄዱ ማዘዛቸው በአካባቢው የመሬት ላይ ጥቃት እንደሚካሄድ እንደሚያመለክት ተገልጿል።
እ.አ.አ በጥቅምት 7 ሐማስ ያደረሰውን ጥቃት ተክትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ በምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ፣ ባለፉት ሁለት ቀናት የተገደሉትን 390 ፍልስጤማውያን ጨምሮ፣ እስካሁን ቢያንስ 20 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል። ቢያንስ ሁለት ሚሊየን ፍልስጤማውያንም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ የሚሰራው (አይፒሲ) ሐሙስ እለት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ እንዳስታወቀው "የቦምብ ድብደባ፣ የመሬት ላይ ዘመቻዎች እና አጠቃላይ ህዝቡ ላይ የተካሄደውን ከበባ" ጨምሮ በጋዛ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት "አሰቃቂ ደረጃ" ላይ የደረሰ አሰከፊ የምግብ ዋስትና እጦት ማስከተሉን አስታውቋል። አሁን ያለው ሁኔታ እና በሰብዓዊ አቅርቦት ላይ የተጣለው ገደብ ካልተሻሻለም፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
አይፒሲ አክሎ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የጋዛ ነዋሪዎች የምግብ አቅርቦታቸውን አሟጠው በመጨረሳቸው አስከፊ ረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙም ጠቅሶ አስጠንቅቋል።
መድረክ / ፎረም