በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ረሃብ በተደቀነባት ሶማሊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል


ረሃብ በተደቀነባት ሶማሊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:22 0:00

ረሃብ በተደቀነባት ሶማሊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው እጅግ አስከፊ ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ ሲሆን አቅመ ደካማ ህፃናትን ህይወት እየቀጠፈ ነው።

በሶማሊያ ዋና ከተማ አቅራቢያ ተፈናቃዮችን እያስተናገዱ ባሉ ሆስፒታሎች እና መጠለያዎች ውስጥ እናቶች እጅግ የተዝለፈለፉና ያለማቋረጥ የሚያለቅሱ ልጆቻቸውን ይዘው ይታያሉ። በርካቶቹ እርዳታ ለማግኘት ረጅም ርቀቶችን ተጉዘው የመጡ ናቸው።

ከሞቃዲሾ ወጣ ብሎ ከገደብ ያለፈ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደሚገኝበት መጠለያ ጣቢያ በቅርቡ የመጡ ሰዎች፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው መሞታቸውንና አቅመ ደካሞችን ጥለው መምጣታቸውን ሲገልፁ ከፍተኛ ጭንቀት ይነበብባቸዋል።

አሚና አብዲ ሀሰን በደቡብ ሶማሊያ ከሚገኝ መንደር ከልጇቿ ጋር ተጉዛ እንደመጣች ገልፃ፣ በምግብ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተጓዳ ህፃንን ጨምሮ የተወሰኑትን ግን ጥላ እንደመጣች ትናገራለች። በዋና ከተማውም የእርዳታ አቅርቦቱ እየተሟጠጠ በመሆኑም አሁንም እንደተራበች ናት። "ሌሎችም እየመጡ ነው" ስትልም ስለሁኔታው አስከፊነት ታስጠነቅቃለች።

በየቀኑ በርካታ ሰዎች ወደእዚህ ስፍራ ይመጣሉ - የመጨረሻ ዘለላ ኃይላቸውን እየተጠቀሙም በአቧራ በተሸፈነው ሜዳ የዛፍ ቅርጫፎችን አጠላልፈው በጨርቅና በፕላስቲክ በመሸፈን መጠለያ ይሠራሉ።

ከኖርዌጂያን ስደተኞች ጉባኤ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቀደም ብለው የመጡ ተፈናቃዮች ወደ ዋና ከተማው ለመድረስ እስከ 19 ቀናት ድረስ ተጉዘዋል። አሁን ከሶማሊያ ዋና ከተማ ወጣ ብለው የሚገኙ መጠለያዎች እጅግ በጣም በደከሙ አዳዲስ ተፈናቃዮች መሞላት በመቀጠሉ፣ የረሃብ አደጋው ዋና ከተማዋንም ሥጋት ውስጥ ከቷታል።

በምግብ እጥረት ለተጎዱ እርዳታ የሚሰጠው ማዕከል እጅግ በተጨነቁ እናቶች እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ልጆች ተሞልቷል። ኦውሊዮ ሀሰን ሳላድ በዚህ ዓመት በድርቅ የተጎዱ አራት ልጆቿ ተራ በተራ ሲሞቱ ተመልክታለች። አሁን ደግሞ እጅግ የደከመውን፣ ያለማቋረጥ የሚያቅሰውን እና ከመንደሯ ጀምሮ ዋና ከተማው ለመድረስ የሚፈጀውን 90 ኪሎ ሜትር ተሸክማው የተጓዘችውን የሦስት ዓመት ልጇን፣ አሊ ኦስማንን አቅፋ ቁጭ ብላለች።

"አስራ ሁለት ልጆች ነበሩኝ ግን አራቱ በዚህ ድርቅ ሞቱብኝ። ከተረፉት ስምንት መሀከል አራቱ በመታመማቸው ትቻቸው መጣሁ። ይህ ትንሹም ደህና አይደለም ስለዚህ እሱን ለማዳን እዚህ አመጣሁት።"

ይህኛውንም ልጇን እንዳታጣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና ታዲያ፣ መንድሯ ውስጥ እህል ለመዝራት እንዳያስችል ሆኖ በደረቀው አፈር ውስጥ ቀብራቸው ስለመጣቻቸው ትንንሽ ልጇቿ ለማውራት ይከብዳታል። በግንቦት ወር ብቻ ወደዚህ ማዕከል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አድጎ 122 ደርሷል።

አንድ በሰብዓዊ እርዳታ ዙሪያ የሚሰራ ቡድን ለአሶስዬትድ ፕሬስ ባጋራው መረጃ መሰረት፣ በዚህ አመት እስከ ሚያዚያ ባለው ግዜ ውስጥ፣ በማዕከሉ የነበሩ ቢያንስ 30 ሰዎች ህይወት አልፏል። በሌላ 'አክሽን አጌንስት ሀንገር በተባለ ተቋም' ስር ባለ ማዕከል ውስጥ ደግሞ ሌሎች ስድስት ሰዎች ሞተዋል።

ተቋሙ በሶማሊያ ውስጥ መስራት ከጀመረ እአአ ከ1992 ጀምሮ የረሃብ ህክምና ማዕከሉ ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የማያውቅ ቁጥር እያስተናገደ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ55 ከመቶ ጨምሯል።

በአጠቃላይ - በዚህ ዓመት እስከ ሚያዚያ ባለው ግዜ፣ በውጭ ክትትል በሚደረግባቸው እና በረሃብ ማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ ተኝተው ይታከሙ የነበሩ ቢያንስ 448 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል። ይህ ቁጥር ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ቡድኖች እና የሀገሩ ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት ሳይመዘገቡ የቀሩ መረጃዎችን በማጠናከር ለአሶስዬትድ ፕሬስ ያጋሩት ሲሆን በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ትክክለኛው ቁጥር እስካሁን በትትክል አይታወቅም።

ባለሥልጣናት መረጃው አይድረሳቸው እንጂ በርካታ ሰዎች እየሞቱ ሲሆን የእርዳታ ሰራተኞች አብዛኛው መረጃ ያልተሟላ ወይም ዘግይቶ የሚደርስ መሆኑን ይገልፃሉ። ትክክለኛውን የሞት ቁጥር ለማወቅ አዳጋች የሆነበት አንዱ ምክንያት የተወሰኑ የደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያን አካባቢ የተቆጣጠረው አክራሪው የአልሻባብ ቡድን እንቅፋት በመሆኑ ነው።

አልሻባብ፣ እአአ ከ2010 እስከ 2012 በሶማሊያ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ የሰጠው ጭካኔ እና ቸልተኝነት የሞላበት ምላሽ ከሩብ ሚሊየን በላይ ሰዎች ለመሞታቸው ምክንያት ሲሆን ግማሾቹ ህፃናት ናቸው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሰጠው እጅግ የዘገየ ምላሽ ሲሆን አሁንም የአደጋ ደወሉ በድጋሚ እያስተጋባ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ለአስከፊ ረሀብ የተጋለጡ ሲሆን በሚያዚያ ወር ተገምቶ ከነበረው 81 ሺህ ቁጥር የበለጠ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ሰኞ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ተቋማቱ እንዳሉት በዚህ ለዚህ ዓመት ከታቀደው እርዳታ 18 ከመቶ ብቻ ነው የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው።

በዚህ ሶማሊያ ብቻዋን አይደለችም። የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ ለአሶስዬትድ ፕሬስ የሰጠው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ድርቅ ባጠቃቸው ክልሎችም ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እርዳታ የተደረገላቸው ህፃናት ቁጥረ ባለፈው ዓመት ከነበረው በ15 ከመቶ ብልጫ አሳይቷል። በሚያዚያ ወር በሀገሪቱ የሶማሌ ክልል እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ከአምስት ሺህ በላይ ህፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ለህዝቡ የሚደርሰው እርዳታ መጠን እንዲቀንስ ተደርጓል።

በየሳምንቱ ወደ ረሃብ ማገገሚያ ማዕከላት የሚገቡ ቁጥር በፍጥነት እያደገ በመሆኑ ዩኒሴፍ 'የቀውስ ጫፍ ላይ ደርሷል' ማለቱን አሶስዬትድ ፕሬስ ገልጿል።

በኬንያም እንዲሁ የድምበር የለሽ ዲክተሮች የእርዳታ ቡድን በአንድ የረሃብ ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ በዚህ ዓመት በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG