በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግስት የቀየሳቸው አዳዲስ የማዋከቢያ ዘዴዎች ምርጫውን ተአማኒነት አሳጡት፤ ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ተቸ


ሂውማን ራይትስ ወች
ሂውማን ራይትስ ወች

«መንግስትና ገዢው ፓርቲ አንድ በሆኑባት፤ ኢትዮጵያ ዜጎች በግዴታ በአባልነት የሚመዘገቡበት አሠራር ይበልጥ አደገኛነት አለው፤»

የኢትዮጵያ መንግስት «መራጮችን በማዋከብና በማስፈራራት፤» ምርጫውን ተአማኒነት አሳጥቶታል፤ ሲል ዓለም አቀፉ የሠብዓዊ መብቶች ተንከባካቢ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ወች በትላንትናው ዕለት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አመልክቷል።

የመንግስቱና የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት ከምርጫው አስቀድሞ፤ «ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ ሥራችሁን ታጣላችሁ፤» የሚለውን ማስጠንቀቂያ ጨምሮ አዳዲስና አስገዳጅ የማዋከቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም የምርጫውን ውጤት በሚፈልጉት አቅጣጫ ለመውሰድ ድምፅ ሠጪው ላይ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ ሲል፥ ዓለም አቀፉ የመብት ድርጅት ወንጅሏል።

ጥናቶቹ እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ በነበሩት ወራትና ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ ያሰባሰባሰባቸውን ቁጥራቸው የበዛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ያስታወቀው ሂውማን ራይትስ ወች ዕርምጃዎቹ፥ ዜጎች የፈቀዱትን በነፃነት የመምረጥ መብታቸውን የነፈጉ መሆናቸውን አስረድቷል።

በአካባቢና በቀበሌ ደረጃ ሳይቀር፤ «በእነኚህ ጊዜያት ውስጥ የተከታተልናቸው፥ ኢህአዴግን አሸናፊ ለማድረግ ሲባል በዜጎች ላይ ይጫኑ የነበሩ ግፊቶችና ወከባዎች ናቸው፤» የሚሉት የድርጅቱ ከፍተኛ የጥናት ባለሞያ ሌዝሊ ሌፍኮ ናቸው።

«አንድ ለአምስት፤» በመባል የሚታወቀው ሲል ሪፖርቱ ያተኮረበት «አዲሱ የኢህአዴግ የመመልመያ ፒራሚድ» አንድ የገዢው ፓርቲ መልማይ ለኢህአዴግ ድምፃቸውን የሚሰጡ አምስት ሠዎችን ማስመዝገብና እንደታለመውም ኢህአዴግን እንዲመርጡ የሚያደርግበትን አሠራር ተንትኗል።

እነኚህ አምስት ሠዎች የመልማዩ ቤተሰብ አባላት፥ ወዳጅ-ጓደኞቹ፤ የሥራ ባልደረቦቹ አለያም ጎረቤቶቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሪፖርቱ ጨምሮ አመልክቷል።

እንዲህ ያለው የምልመላ ዘዴ፥ ግዴታና ወከባ ባይኖርበት፤ በምርጫና በፍቃድ የሚፈፀም ቢሆን ኖሮ፥ ምናልባትም በራሱ ብቻውን ይህን ያህል ግዙፍ ፈተና ባልሆነ ነበር የሚሉት ሚስስ ሌፍኮ «መንግስትና ገዢው ፓርቲ አንድ በሆኑባት፤ ኢትዮጵያ ዜጎች በግዴታ በአባልነት የሚመዘገቡበት አሠራር ይበልጥ አደገኛነት አለው፤»ብለዋል። ኢትዮጵያ ግን እንዲህ ያለው አሠራርና አቀራረብ ጉዳዩ ሌላ ነው፥ ብለዋል።

ዋናው የኢህአዴግ ተቃውሞን ማፈኛ መሳሪያ ቀበሌ ነው፤ የሚሉት የሰብዓዊ መብት ጥናት ባለሞያዋ፥ አያይዘውም፥ ዜጎች የሚያገኟቸው የመንግስት አገልግሎቶች ለገዢው ፓርቲ ባለ ቅርበትና ድጋፍ መወሰናቸው ሌላው ችግር መሆኑን በጥናታቸው እንደረሱበት አመልክተዋል።

ዋና ዋናው ተቃዋሚ ቡድኖች ሙሉ በሙሉ በምርጫው የተሸነፉበትና፥ ኢህአዴግ መቀማጫዎቹን ጠቅልሎ መውሰዱን የሚያመለክቱ የቅድሚያ ውጤቶች መሰማታቸው የሚሰጠውን ትርጓሜም ሲያስረዱ፤ ድርጅታቸው በጥናቱ ያመላከተውን የሚደግፍና፤ ምርጫውን የታዘበው የአውሮፓ ህብረት በዛሬው ዕለት ይፋ ካደረገውም ጋር የተስማማ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሂውማንራይትስ ወች በትላንትናው ዕለት ይፋ ያደረገውን ይሄንን ሪፖርት ውድቅ አድርጓል።

XS
SM
MD
LG