በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎቹ ላይ አዲስ የኮፒውተር ሥለላ ውንጀላ ቀረበበት


ፌሊክስ ሆርን እና አቶ ጃዋር መሀመድ
ፌሊክስ ሆርን እና አቶ ጃዋር መሀመድ

የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ በአዲስ መልኩ የተጠናከረ የኮምፒውተር ሥለላ እያደረገ መሆኑን የመብት ድርጅቱ ሒውማን ራይትስ ወች አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ በአዲስ መልኩ የተጠናከረ የኮምፒውተር ሥለላ እያደረገ መሆኑን የመብት ድርጅቱ ሒውማን ራይትስ ወች አስታወቀ።

ጥቃቱ ያነጣጠረው በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኦሮሞና ሶማሊ ተወላጅ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ አደራጆች፣ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች ላይ መሆኑን የመብት ድርጅቱ ዘገባ ይገልፃል።

በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች፣ ዩናይትድ ስቴይትስ አውሮፓና በአውስትራሊያም ጭምር የሚኖሩ ተቃዋሚዎች፣ የተቃውሞ የመገናኛ ብዙሃንና የለውጥ አቀንቃኞች ላይ ማነጣጠሩን ትናንት ይፋ ባደረገው የምርመራ ዘገባ ዘርዝሯል።

ፌሊክስ ሆርን የመብት ድርጅቱ መረጃ አጠናቃሪ ናቸው። የሒውማን ራይትስ ወች ዘገባ ምንጭ በቶሮንቶ ካናዳ መሰረቱን ያደረገ ሲትዝን ላብ የተባለ የጥናት ቡድን ያወጣው ቴክኒካዊ ሪፖርት መሆኑን ያስረዳሉ።

“ጠንቀኛ የኮምፒውተር መሰለያ ዘዴው በእስራዔላዊ ኩባንያ የተሰራ ነው። እንዲህ ነው የሚሰራው። የድረገጹ ሰላይ በአንድ ግለሰብ ኮምፒውተር ላይ ከወረደ፤ ለኢትዮጵያ መንግስት ያለውን መረጃ በሙሉ አሳልፎ ይሰጣል” ብለዋል።

የኮምፒውተር የሥለላ ተውሳኳን በሚታወቁ ሰዎች ኢሜይል አስመስለው እንደሚልኩና በኮምፒውተሩ ከተጫነች በኋላ መረጃና ቁጥጥሩን አሳልፋ ትሰጣለች።

“የተላኩ ኢሜሎችን፣ የተከፈቱ ድረ-ገጾችን፣ በስካይፕ የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ይቀዳል፣ ከርቀት ካሜራውን ተጠቅመው ማየት፣ ማይክሮፎኑን ከፍተው ንግግርን ማዳመጥና ክንውኖችን መመልከት ያስችላቸዋል። ስለዚህ በዚህ ኮምፒውተር ዙሪያ የሚደረጉ ነገሮችና ያሉ መረጃዎችን የኢትዮጵያ መንግሥት ሊመለከታቸው ይችላል።”

ሒውማን ራይትስ ወች የሲትዝን ላብን ጥናት ተምርኩዞ ባወጣው ዘገባ እንደዚህ አይነት ጥቃት የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያንና የሌሎች ሀገር ዜጎች መንግሥቱን የሚቃወሙ ናቸው።

የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ ላይ በተደጋጋሚ የኮምፒውተር የሥለላ ተውሳክ ተልኮበት ነበር።

“ሲትዝን ላብ ባደረገው ጥናት መሰረት የጃዋርን ኮምፒውተር ለመቆጣጣር በርካታ ጥረት ተደርጎ ነበር። የሚያውቃቸው ሰዎችን ኢሜይል ተመስለው የሚመጡ መልእክቶች ደርሰውታል።”

የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ የኮምፒውተር ሥለላ ጥረቱ በእርሱ የተሳካ ባይሆንም፤ ሌሎች አጋሮቹና የለውጥ አራማጆች ላይ ግን የተሳካ መሆኑን አስታውቋል።

“እኛ ሚዲያ ስለሆንን በተደጋጋሚም ሙከራ ስለሚደረግብን ጠንከር ያለ የሴኪውሪቲ ሲስተም ነው ያለን። ሌሎቹን ግለሰቦች ግን ገብተው እየተከታተሏቸው ነበሩ” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀድም መንግሥቱን የሚቃወሙ ድምፆችን በሳተላይት የሚያስተላልፈው ኢሳት ቴሌቭዥንና ሰራተኞች ላይ የኮምፒውተር የስለላ ተውሳክ ልኳል በሚል በድርጅቱና በመብት ተሟጋቾች ሲተች ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሥለላ አጥቅቷል በሚል ውንጀላ የሚቀርብበትን የመገናኛ ብዙሃንና ሠራተኞች ላይ ሁከትን በማነሳሳት የሽብር ክስ መስርቶባቸዋል።

የሒውማን ራይትስ ወቹ ፌሊክስ ሆርን እነዚህ ጥቃቶችና የፍርድ ቤት ክሶች በኢትዮጵያ አንድ አይነት ድምፅ ብቻ እንዲሰማ መንግሥቱ ካለው ፍላጎት የመነጩ ናቸው ይላሉ።

“ጃዋርም ሆነ ኢሳትና /OMN/ የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጆች አለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። መንግሥቱን ይቃወማሉ። ያ ግን ወንጀል አይደለም። አሸባሪዎች ናቸው ተብሎ ሊከሰሱ አይገባም።” ብለዋል።

በኮምፒውተር የሚደረጉ ሥለላዎችን አስመልክቶ ሕገወጥ ወይንም ክልክል የሚያደርግ ሕግ ወይንም ዓለምቀፍ ሥምምነት አለመኖሩን የሂውማን ራይት ወቹ ፌሊክስ ሆርን ያስረዳሉ።

ሆኖም አንዳንድ ተቃዋሚዎችና ግለሠቦች ሁኔታው በሕግ የሚቆምበትን መንገድ እያፈላለጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ ምላሻቸውን እንዳገኘን እናቀርባለን።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎቹ ላይ አዲስ የኮፒውተር ሥለላ ውንጀላ ቀረበበት
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:16 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG