በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ የተማሪዎች መታሰር


የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የመንግሥቱ ወታደሮች በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ በወሰዷቸው የኃይል እርምጃዎች በርካቶች ተጐድተዋል አለ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተማሪዎች ከፖለቲካና ጐሣ ጋር የተያያዙ ጥቃቶችን በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ማድረሳቸውን አስታወቀ።

ከታሠሩት ውስጥ አራቱ ወደ አዲስ አበባ ተይዘው መወሰዳቸውንም ድርጅቱ አስታውቆ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እንዲያበቃ የታሠሩት ባስቸኳይ እንዲፈቱና የተቋረጠው ትምህርት እንዲቀጥል ያደርግ ዘንድ ለመንግሥት ተማጽኖ አቅርቧል።

ይህን የሰኞውን አስቸኳይ የተማጽኖ ጥሪ ያወጣው ዋና ጽሕፈት ቤቱን በቶሮንቶ ካናዳ ያደረገው የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ የተባለው የመብቶች ተሟጋች ድርጅት ሲሆን ኃላፊው አቶ ጋሩማ በቀለ ዋቀሣ ይባላሉ።

ድርጅቱ በተለይ በተለያዩ ጊዜአት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በፖሊስ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተወሰዱ በኋላ የደረሱበት ጠፍቷል የተባሉትን የአራት ተማሪዎች ስም ዝርዝር በመግለጫው ያወጣ ሲሆን፥ እነርሡም፥ ግርማ ቱሩና እና ደቻሣ ዊርቱ ሞሲሣ ከሓሮማያ ዩኒቨርሲቲ፥ ጋዲሣ ረጋሣ ከሐዋሳ፥ ፈይሣ ፉፋ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ መሆናቸውን አስታውቋል። የተያዙባቸውን ቀናትም አስቀምጧል።

ከዚህም በተጨማሪ ከብጥብጡ በኋላ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ተማሪዎች የመታወቂያ ካርዶቻቸውን እንደተነጠቁና ለጊዜውም ቢሆን በሁኔታው የተደናገጡ ከትግራይ ተወላጆች በስተቀር የቀሩት ተማሪዎች በሙሉ ካምፓሱን ለቅቀው ለመሸሽ መገደዳቸውን ካካባቢው ዜና ተላላኪዎቹ መረዳቱንም ድርጅቱ ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ፥ ያካባቢው ባለሥልጣናት ከትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ወደየዘመዶቻቸው መመለስ የሚፈለጉ ተማሪዎች በየትኛውም አቅጣጫ እንዳይወጡ መከልከላቸውንም ድርጅቱ ጨምሮ አስረድቷል።

የድርጅቱ ዜና አቅራቢዎች እንደገለጹለት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኞቹ ተማሪዎች ወደ ጂማ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ አግኝተዋል።

የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ነው ያለው የጥቃት ዘመቻ ባስቸኳይ ይቆም ዘንድ ተማጽኖውን ለአትዮጵያ መንግሥት ከማቅረቡም በላይ ተቆርቋሪዎች ጉዳዩን በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኤምባሲ ተጠሪዎች በሙሉ እንዲያሳውቁም ጠይቋል።

መግለጫውን ጄኔቭ ለሚገኘው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኰሚሽን፥ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኰሚሽነር-ዩኤንኤችሲአር፥ ባንጁል-ጋምቢያ ላለው የአፍሪቃ የሰብዓዊ መብቶች ኰሚሽን፥ ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ለሒዩመን ራይትስ ዋች በግልባጭ አስታውቋል።

በዚህ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ምላሽ ለማግኘት ወደ አካባቢው ባለሥልጣናት ቢሮ እንዲሁም አዲስ አበባ ወደ ፌዴራሉ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ያደረግናቸው የስልክ ጥሪዎች ለዛሬ ምላሽ አላገኙም። ጥረታችን ነገም ይቀጥላል።

ዘገባውን ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG