በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ የመብት ተሟጋቾች ጠየቁ


ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት
ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት

ቤጂንግ በርካታ የዊገር ማኅበረሰብ ተወላጆችን በማሰር የሚደርስባትን ክስ ለማጣራት በቅርቡ ወደ ሺን ጃንግ ተጉዘው የነበሩት የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት ቤይጂንግን ሳያወግዙ ቀርተዋል በሚል ከፍተኛ ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው። ከኃላፊነታቸው እንዲለቁም ተጠይቀዋል።

ባሸሌት ወደ ቻይና ባደረጉት ጉዞ ቤይጂንግ በሺንጃንግ ግዛት በሚገኙ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ወደ 2 ሚሊየን ዊገሮችን በግዳጅ ማሰሯን ሳያወግዙ ቀርተዋል በሚል ተቺዎች ከሰዋቸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ 50ኛ ስብሰባውን ሊያካሂድ በተዘጋጀበት ወቅት፣ ከ230 የሚበልጡ የመብት ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ ከፍተኛ ኮሚሽነር ባሸሌት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን ቤይጂንግ በዊገሮች፣ ቲቤቶች እና ሌሎች አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች ላይ የምታደርሰውን ጭቆና በማለባበስ ከሰዋቸዋል።

ባሸሌት በጉብኝታቸው የመብት ጥሰቶቹን ከማጋለጥ ይልቅ ቤጂንግ በፕሮፖጋንዳ ድል እንድታደርግ ረድተዋል ተብለዋል። መንግሥት ለፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ተጠያቂ ለማድረግ ያጋጠማቸውን ብርቅዬ ዕድልም አባክነዋል በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል።

ባሸሌት ለቀረበባቸው ትችት ምላሽ ባይሰጡም ባለፈው ወር ባካሄዱት የቻይና ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ግን ጉዞአቸው ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ስለሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለመነጋገር እና ለቀጣይ ንግግሮች መንገዱን ለመክፈት መሆኑን ገልፀው ነበር።

በቻይና ላይ ልስላልሴ አሳይተዋል ለተባለው ቅሬታም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል በሺንጃንግ በሚደርሰው አፈና ዙሪያ ከቻይና መሪዎች ጋር በግልፅ መነጋገራቸውን ገልፀው ራሳቸውን ተከላክለዋል።

የመብት አቀንቃኞች ባቸሌት ለረጅም ግዜ ሲጠበቅ የቆየውን በቻይና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የተዘጋጀውን ሪፖርት እንዲያወጡ እየወተወቷቸው ቢሆንም፣ የጉባኤው ፕሬዝዳንት ፌድሪኮ ቬሌጋስ ሪፖርቱ ገለልተኛ መሆኑን እና የማውጣት ኃላፊነቱ የጉባኤው ሳይሆን የዋና ጸሐፊው መሆኑን ገልፀዋል።

XS
SM
MD
LG