በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሂዩማን ራይትስ ዋች ስለ አማኑኤል ወንድሙ ግድያ


“በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኃይሎች አማኑኤል ወንድሙ የሚባል የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በአደባባይ በጥይት መትተው ገድለዋል” ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። “በአማኑኤል ላይ የተፈፀመው ግድያ በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች በሚፈፅሟቸው ድርጊቶች ተጠያቂነት አለመኖሩን የሚያሠምርበት ነው ሲል” ቡድኑ ከስሷል።

"በምዕራብ ኦሮምያ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ውስጥ ባለፈው ግንቦት 3/2013 ዓ.ም. አማኑኤል ወንድሙን የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር አውለው ድብደባ ፈፅመውበታል" ያለው የቡድኑ መግለጫ የከተማዋ አስተዳደር በማኅበራዊ መገናኛ ያወጣው ቪዲዮ ላይ የፀጥታ ኃይሎች ደም በደም የሆነውን እና አንገቱ ላይ የታሰረ ሽጉጥ ደረቱ ላይ የተንጠለጠበትን አማኑኤልን ሲያዋክቡት መታየቱን እና በዚያው ዕለት በጥይት መገደሉን አውስቷል።

በማስከተልም በቀጠሉት ሣምንታት ባለሥልጣናቱ የአማኑኤልን ቤተሰብ አባላት ጨምሮ የደምቢ ዶሎ ነዋሪዎችን ሲያስፈራሩና ሲያስሩ እንደነበር መግለጫው አመልክቷል።

የ"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወጣቱን ያለአንዳች የፍርድ ሂደት መግደላቸው ለሰው ህይወት ያላቸውን የሚያስደነግጥ ደንታ ቢስነት የሚያሳይ ነው ያሉት የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሌቲሽያ ባደር "የፀጥታ ኃይሎቹና የከተማዋ አስተዳደር ባለሥልጣናት ይህን የሚዘገንን አድራጎት በቪዲዮ ቀርፀው ያሠራጩበት ጭካኔ ከህግ በላይ ነን፤አንጠየቅም የሚል ዕምነት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አማኑኤልን በመሳሰሉ የኦሮምያ ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ለማስቆም ከልባቸው ቁርጠኛ መሆናቸውን ማሳየት እና ተጠያቂዎቹን ለፍርድ ማቅረብ አለባቸው” ሲሉ ሌቲሲያ ባደር አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ግን አድራጎቱ እንደተፈፀመ የቄለም ወለጋ ዞን ፖሊስ ፅህፈት ቤት የፀጥታ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኢንስፔክተር አህመድ ያስን አማኑኤል ላይ “እርምጃ” መወሰዱን አረጋግጠው “ሲሳይ ፊዳ የሚባል ጋዜጠኛን ተኩሰው በመግደል ከተጠረጠሩት መካከል መሆኑን በአንደበቱ አረጋግጦልናል" ብለዋል።

በወንጀሉ ተጠርጥሮ መገደሉ የተገለፀው የአማኑኤል ወላጅ አባት አቶ ወንድሙ ከበደ ግን ልጃቸው ፖሊስ የሚለውን ወንጀል “ፈፅሟል” ብለው እንደማያምኑ አመልክተው" ልጄ በወንጀልን ተጠርጥሮ እንደሆነ እንኳ ከሚገደል በህግ ሊዳኝ ይገባ ነበር" ብለዋል።

የዞኑ ፖሊስ ምክትክ ኃላፊ ኢንስፔክተር አህመድ ያሲን ግን አማኑኤል የተገደለው ከፖሊስ ለማምለጥ ሲሞክር ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን (ኢሰመኮ) በዕለቱ ባወጣው ባወጣው አጭር መግለጫ "በደምቢ ዶሎ ከተማ የአማኑኤል ወንድሙ ያለፍርድ ውሳኔ መገደል አሳስቦኛል” ሲል አሳውቆ ጉዳዩ ተጣርቶ አግባብነት ያለው እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቦ ነበር።

XS
SM
MD
LG