በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦጋዴን ውስጥ ተፈፅሟል ላለው ጥቃት ሂዩማን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ መንግሥትን በግድያና በመብቶች ረገጣ ከሰሰ


ሌስሊ ሌፍኮው - የሂዩማን ራይትስ ዋችን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር
ሌስሊ ሌፍኮው - የሂዩማን ራይትስ ዋችን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር

በኦጋዴን የራቅዳና አካባቢዋ ሁከትና የመንግሥት ወገን በሆኑ ኃይሎች የጥቃት እርምጃ ላይ የሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጫ ሰጠ፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት አካላት የሆኑ የልዩ ፖሊስ ኃይሎች ባለፈው መጋቢት ኦጋዴን ውስጥ ባካሄዱት ዘመቻ አሥር ሰዎችን እዚያው ገድለዋል” ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች ትናንት ከስሷል፡፡

የልዩ ፖሊስ ኃይሉ አድርሶታል ስለተባለው ግድያና ሌሎችም የክፋት አድርጎቶችን የሚመለከተው ዝርዝር መግለጫ የወጣው የሂዩማን ራይትስ ዋች እውነት ፈታሽ ቡድን ወደ አጎራባቿ ሶማሊላንድ ባለፈው ወር ውስጥ ከተላከ በኋላ እንደነበረ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዋችን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ በሶማሌ ክልል ጋሻም ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ራቅዳ ቀበሌ የተፈጠረው ለብዙ ሕይወት መጥፋትና ለብዙ ሰው መጎዳት መንስዔ የሆነው መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም ፈፅሞታል ያሉት ግድያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“እኛ ባሰባሰብነው መረጃ መሠረት - አሉ ሌፍኮው - መጋቢት 7 ቀን በራቅዳ ቀበሌ በአንድ የልዩ ፖሊስ ኃይል አባል የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ የቀበሌው ሰዎች መሣሪያ አንስተው በወሰዱት የበቀል እርምጃ ሰባት የልዩ ፖሊስ አባላትን ገደሉ…”

ያንን አጋጣሚ ተከትሎ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሌፍኮው ሲናገሩ “በተከታዩ ቀን የልዩ ፖሊስ አባላት በአካባቢው ባሉ አራት የተለያዩ ቀበሌዎች ተሠማሩና እጅግ የከፉ የረገጣ አድራጎቶችን ፈፀሙ” ብለዋል፡፡

እነዚህ አድራጎቶች በሥፍራው የተወሰዱ የነፃ እርምጃና የግድያ አድራጎቶችን፣ እጅግ በርካታ ቁጥር ባላቸው ቤቶችና ሱቆች ላይ ተፈፀሙ የተባሉ ዘረፋዎችን የሚያካትቱ እንደሆኑ ሌፍኮ አክለው ተናግረዋል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዋች ስለተፈጠረው ሁኔታ የሶማሌ ክልልም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሣካለት ሌፍኮ አመልክተዋል፡፡

ሌስሊ ሌፍኮን ያነጋገረው የቪኦኤ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ባልደረባም ተመሣሣይ ሙከራዎችን አድርጎ እንደነበርና የሚያነጋገረው ሰው አለማግኘቱን ዘግቧል፡፡

ለተጨሪና ዝርዝር መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG