በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሂዩማን ራይትስ ዋች አዲስ ክሥና የኢትዮጵያ መንግሥት


ሂዩማን ራይትስ ዋች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አዲስ ክሥ አውጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሂዩማን ራይትስ ዋች “ዋሽቷል” ይላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በጀመረው የመንደር ምሥረታ ፕሮግራም በጋምቤላ አካባቢ ከፊል አርብቶ አደር ዜጎችን በግድ እያፈናቀለ ያነሣል፣ ጥቃት ያደርሣል፣ ያደርሣል ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች ትናንት ባወጣው ሪፖርት ከሰሰ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ክሱ መሠረተ-ቢስና የሂዩማን ራይትስ ዋች የተለመደ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ይላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በመንደር ምሥረታ ፕሮግራሙ በምዕራብ ኢትዮጵያ ሰባ ሺህ የጋምቤላ ብሔረሰብ አባላትን በኃይል እያፈናቀለ እንደሚያሰፍር ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ያስታወቀው ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ነበር፡፡

ቡድኑ “እዚህ ተቀምጦ ሞትን መጠበቅ” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርቱ በጋምቤላ የተካሄደውን የመንደር ምሥረታና የሠፈራ መርኃግብር የአንድ ዓመት አፈፃፀም መገምገሙን አመልክቷል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ ዛሬ ከለንደን በስልክ ቪኦኤ መግለጫ የሰጡት ጥናቱን ያካሄዱትና ሪፖርቱንም የፃፉት የሂዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ሴሊክስ፣ የመንደር ምሥረታው ሃሣብ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚሠሩበት እንደሆነ ከመነሻው የኢትዮጵያ መንግሥት ተናግሮ እንደነበረ ጠቁመው እርሣቸው ያዩት ግን የተገላቢጦሹን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“የእኛ ጥናት ያገኘው የማሥፈሩ ሥራ እየተካሄደ ያለው በፍቃደኝነት አይደለም፤ ይገደዳሉ፤ ለመሄድ ፍቃደኛ ያልሆኑት ወይም ለምን የሚሉት በፖሊስና በወታደር ይደበደባሉ፣ ይታሠራሉ፤ ይንገላታሉ፡፡” ብለዋል ሆርን፡፡

በጋምቤላ የነባሮቹ የኙዌርና የአኝዋክ ብሔረሰቦች አባላት እየተፈናቀሉ ከሰባ ሺህ በላይ ሄክታር ለውጭ ኢንቬስተሮች መሰጠቱን የሚጠቁመው ሂዩማን ራይትስ ዋች ተነሺዎቹ በሠፈሩባቸው መንደሮች ውስጥ የመሠረተ ልማት አውታር እንዳልተዘረጋና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዳልተከፈቱ ይናገራል፡፡ ሠፋሪዎቹ በምግብ እጦትም እየተቸገሩ መሆናቸውንና ምግብ ሲፈልግ ሞቷል የተባለ ሰው ማየታቸውንም የጥናቱ አቀናባሪና የሪፖርቱ ፀሐፊ ሴሊክስ ሆርን አመልክተዋል፡፡

የግዙፎቹ ዓለምአቀፍ ለጋሾች ገንዘብም ላልታሰበለት ለመንደር ምሥረታው ተግባር በእጅ አዙር እንደሚውል ድርጅቱ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ክሱ መሠረተ-ቢስና የሂዩማን ራይትስ ዋች የተለመደ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ብሏል፡፡

“ሂዩማን ራይትስ ዋች በመሬት መስጠትም ሆነ በሠፈራው ፕሮግራም ላይ ያወጣው ሪፖርት መሠረተ በሌላቸው ጉዳዮች ላይ የቆመ ነው፡፡ በየዓመቱ በተከታታይ የሚያካሂዱት ዘመቻ አካል ነው፡፡ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ያወጧቸውን ሪፖርቶች ብትመለከቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች ስም የማጥፋት ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡ ለእኛ ጉዳዩ የሰብዓዊ ጉዳይ ሳይሆን የርዕዮተ-ዓለምና የፖለቲካ ጥቅም የተንፀባረቀበት ጉዳይ ነው፡፡” ብለዋል የኢትዮጵያ መንግሥት ቃልአቀባይ አቶ በረከት ስምዖን፡፡

ዝርዝሩን ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG