በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሂዩማን ራይትስ ዋች ኢትዮጵያ ላይ ያወጣው ዘገባ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል


ለጋሽ አገሮች ከሚሰጡት በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር አብዛኛው የገዢውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ለማጠናከር ነው የሚውለው ይላል ሂዩማን ራይትስ ዋች።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ባለፈው ጥቅምት 10 ያወጣው ዘገባ የኢትዮጽያ መንግሥት ከለጋሾች የሚሰጠውን የልማት እርዳታ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን ለመጨቆን ይጠቀምበታል ሲል ይከስሳል።

በሪፓርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ መልስ አልሰጡም። ሆኖም መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዌብ ሣይት ላይ ባተመው መግለጫ “በዘመነኛ ቅኝ አገዛዝ ስሜት የተሸፈነ ገደብ የለሽ ትዕቢት” ሲል የሰብአዊ መብት ድርጅቱን ዘገባ አሽሟጧል።

የ 25 ለጋሽ አገሮች ስብስቡ ዳግ ቀደም ብሎ በዚህ ዓመት እራሱ ያካሄደው ምርመራ “የእርዳታ እህልን ለተቃዋሚዎች መጨቆኛ ማዋል ሰፊና ሆን ተብሎ የሚደረግ ለመሆኑ ያገኘው ማስረጃ የለም” ብሏል።

የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮግራም ክፍተኛ ተመራማሪ ሌዝሊ ሌፍኮ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ የለጋሽ አገሮች ማህበረሰብ መንግሥት እርዳታውን ያላግባብ እንደሚጠቀም ማጋለጥ ይፈራሉ ብለዋል።

“ጥናቱን አካሂደን ሪፖርቱን ይፋ ከማድረጋችን በፊት ከብዙዎቹ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተናል። ብዙዎች በስውር የኢትዮጵያ መንግሥት ጨቋኝ እንደሆነ ይስማማሉ። በግል ስታነጋግራቸው ጨቋኝ ነው ይላሉ፤ ይህን ግምገማ በይፋ ለመስጠት ግን ድፍረት ይጎድላቸዋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ መሪ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ቀድሞ በዓለም ባንክ በዳይሬክተርነት ያገለገሉና ለብዙ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው የሠሩ ናቸው። “ባለፈው ግንቦት ምርጫ ገዥው ፓርቲ ይበትነው የነበረ ከፍተኛ ገንዘብ የእርዳታ ገንዘብ እንደሚመዘበር ለለጋሽ አገሮች ጠቋሚ ሊሆን ይችል ነበር” ብለዋል።

በምርጫው ወቅት ለፖለቲካ ወገንተኝነት ገንዘብ እንደልብ ይከፈል እንደነበርና “ገንዘቡ ያልደረሳቸው የተገለሉት ብቻ ናቸው” ማለታቸው ተዘግቧል። ለዝርዝሩ የፒተር ሃይንላይንን ዘገባ ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG