በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰመጉ የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲቋረጥ ተደረገ


የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ዓርማ
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ዓርማ

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ለዛሬ፤ ዕሁድ ጥቅምት 13/2009 ዓ.ም ያዘጋጀውና እያካሄደ የነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብር ሳይጠናቀቅ በፀጥታ ኃይሎች ተቋርጧል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ዳይሬክተር አቶ ብፅዓተ ተረፈ፣ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ቁምላቸው ዳኘ፣ ጠበቃው እና የሰመኮ አባሉ አቶ አምሃ መኮንንና ሌሎችም የጉባዔው መሪዎች “የመንግሥትን ስም እያጎደፋችሁ ነው” የሚል ተግሣፅ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን ሥፍራው ላይ የነበረው የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን መለስካቸው አምሃ ገልጿል፡፡

ደሣለኝ ሆቴል ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን መርኃግብር ቦታው ላይ ተገኝተው እንዲቋረጥ ያደረጉት ሲቪል የለበሱና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሆኑ የፀጥታ ሰዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

ፕሮግራሙ እንዲካሄድ ፍቃድ የተጠየቀውም የተፈቀደውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ እንደነበረ ታውቋል፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብሩ የተዘጋጀው መስከረም 28/1984 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ - ኢሰመጉ" በሚል ስያሜ የተመሠረተውንና በኋላ ስሙ በመንግሥት ትዕዛት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ - ሰመጉ ሆኖ እንዲለወጥ የተደረገውን የሃገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ሃያ አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ውስጥ የምሣ ግብዣ፣ የበጎ ፍቃድ ልገሣ፣ የሰመጉ ዓርማ ያለበት ካናቴራና ሌሎችም ቁሣቁስ ሽያጭ፣ የሥዕል ጨረታ ተካትተው እንደነበረ ታውቋል፡፡

ቁጥሩ እስከመቶ የሚደርስ ተሣታፊ ተገኝቶበታል የተባለው ይህ ሥነ-ሥርዓት እንዲቋረጥ የተደረገውና ታዳሚውም የተበተነው ሰመጉ ያሰባሰበው ገንዘብ መጠን ሳይገለጥ ነው፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

የሰመጉ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተቋረጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:26 0:00

XS
SM
MD
LG