በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ውሳኔ 128 ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?


ውሳኔ 128
ውሳኔ 128

የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታና አጠቃላይ አስተዳድር ከዩናይትድ ስቴይትስ ፖሊሲ ጋር ለመቃነት ያለመው ውሳኔ 128 በዩናይትድ ስቴይትስ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ፊት ትናንት ምሽት ቀርቦ ያለምንም ተቃውሞ ጸድቋል።

የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታና አጠቃላይ አስተዳድር ከዩናይትድ ስቴይትስ ፖሊሲ ጋር ለመቃነት ያለመው ውሳኔ 128 በዩናይትድ ስቴይትስ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ፊት ትናንት ምሽት ቀርቦ ያለምንም ተቃውሞ ጸድቋል።

በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ክብር የቆመ ሁሉን አቀፍ አስተዳድር እንዲኖር ለማገዝ ያለመ እንደሆነ በመቅድሙ ይገልጻል ውሳኔ 128።

በዴሞክራቶችና ሪፐብሊካን አባላት ድጋፍ የጸደቀው ውሳኔ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሚታዩ ያላቸውን የመብት ጥሰቶችና የዴሞክራሪያ አስተዳድር በደሎች የዘርዘረና፤ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የደረሱ ግድያወችን የሚያወግዝ ነው። ህጉን ያረቀቁት የኒውጀርሲው ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ውሳኔው ለድምጽ ከመቅረቡ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ይዞታውና አስተዳድሩ የቆመላቸው መርሆዎች፤ የዜጎችን ጥቅም የሚያስከብሩ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። ውሳኔው አሉ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት በስድስት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ድጋፍ የተሰጠውና የመብት ጥሰቶች የተዘረዘሩበት ነበር ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥና የምጣኔ ሀብት ተሳትፎ እድል በጠየቁ ወጣቶች በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ለረጂም ጊዜ የዘለቁ ሰልፎች እንደተካሄዱባት የመብት ድርጅቶቹ በድጋፍ ደብዳቤያቸው አስቀምጠዋል። መንግስቱ ግን ከልክ ያለፈ ሃይል በመጠቀም ከ1ሽህ በላይ ዜጎቹን ገድሏል።” ብለዋል ክሪስ ስሚት።

በትናንትናውለት የኦክሎሃማው ሴናተር ጄምስ ኢንሆፍ በዋሽንግተን የፖለቲካ ክበቦች በሚነበበው ዘ-ሒል ላይ ባሳተሙት ጽሁድ፤ ውሳኔ 128ን የምክር ቤቱ አባላት ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቀው ነበር። ለዚህም የሰጡት ምክንያት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አቢይ አሕመድና አስተዳድራቸው ለውጥ እንዲያመጡ እድል እንስጥ የሚል ነበር።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኗ ውሳኔ 128ን ማጽደቅ ተገቢ ያልሆነና ጊዜውን ያልጠበቀ ነው ሲሉ ለኮንግረስ አባላት ደብዳቤ የጻፉት በዩናይትድ ስቴይስት የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ናቸው።

የኒውጀርሲው ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ትናንት ማምሻውን ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የሚመጡ የአመራር ለውጦች ለሕዝቡ ያመጡት ፋይዳ የለም ብለዋል።

“በኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግርን ተከትሎ በተፈጠሩ ሁኔታዎ የተረዳንው ብዙ ቃል የሚገባና “የተገቡት ቃላት ግን የማይሟሉባቸው እንደሆኑ ነው።” ብለዋል ኮንግረስማን ስሚት። “ተቃዋሚዎችን ለውይይት እየጠሩ በጎን ስልጣን ማጠናከር ነው ስራቸው፤ ይሄ ዳግም ሊፈጠር አይችልም። ስለዚህ ይሄ ውሳኔ በእያንዳንዳችን የህዝብ ተወካዮች ሊደገፍ ይገባዋል” ብለዋል።

በአዳራሹ ዙሪያ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን በውሳኔ 128 መጽደቅ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ኢትዮጵያዊያኑ የዘርና የፖለቲካ ልዮነቶቻቸውን አቻችለው ለጋር ግብ መስራታቸውን ነው የሚናገሩት፤ በድርጅትም እንደ-ግለሰብ።

ቴዎድሮስ ትርፌ በሰሜን አሜሪካ የአማራ ማሕበር ወኪል ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ የአማራ ድርጅቶችን በሰሜን አሜሪካ ያስተባበረው አድማስ አካል ናቸው።

“ግባችን በዚህ የሕግ-መምሪያው ምክር ቤት ውሳኔ 128 ማለፍ ያገኘንውን ሀይል ይዘን በሴኔቱ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እንዲያልፍ አጋር በማፈላለግ እንሰራለን። ከዚያም በተጨማሪ ውሳኔው ያካተታቸው የመፍትሄ ሀሳቦች በመንግስቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከኮንግረስ አባላት ጋር አብረን እንሰራለን። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዲተገብረው፣ USAID እንዲተገብረው፤ የገንዘብ ምንስቴርም እንዲሁ ተግባራዊ እንዲያደርግ እንሰራለን። የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን በበኩሉ እንዲያስተካክል የቀረቡ ሃሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርግ እንሰራለን፤ ይህንንም ለኮንግረስ አባላት በማሳወቅ እንሰራለን።”

ህጉ እንዲጸድቅ በቅንጅት ከሰሩት በርካታ ድርጅቶች አንዱ የኦሮሞ አድቮከሲ አልያንስ ሲሆን ድርጅቱን ወክለው የምስክርነት ቃል ሲሰጡና ኮንግረስን ሲወታውቱ የቆዩት አቶ ግርማ ታደሰ በተቀናጀ ስራ ውጤት እንደተገኘ ተናግረዋል “የአማራ አሶሲየሽን ኦፍ አሜሪካ የሚባል፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሒውማን ራይትስ ወች፣ ሌሎች የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት…በጋራ በቅንጅት ስንሰራ ነበር” ብለዋል። “በጣም የረጂም ጊዜ ስራ፣ የተቀናጀ ስራ፣ ብዙ ነገር የተማርንበት ነው። ግን ዛሬ በመሳካቱ በጣም እድለኛ ነን”

ይሄን የውሳኔ ሀሳብ ያረቀቁት የኒውጀርሲው ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ከዚህ በፊት እንደተናገሩት ውሳኔ 128 ለኢትዮጵያ መንግስት እራሱን እንዲታዘብ ከፊቱ የተቀመጠ መስታዎት ነው። ሌሎች እንደዚህ ነው የሚያዩዋችሁ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። አላማውም እራሳቸውን ፈትሸው ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ውሳኔ 128 ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:32 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG