ከታቀደለት ጊዜ ወደ ሰዓት ገደማ ዘግይቶ ነበር የተጀመረው ስብሰባ «በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” ላይ ከኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያ ጋር ለመወያየት የተዘጋጀ መድረከ ነበር።
በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ መንግሥት አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩ አጠር ያለ የማስተዋወቅ ገለጻ በኋላ፣ ስለ ፭ ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን ገለጻ ሊቀጥል ሲል፣ አንድ ድምፅ ከሕዝቡ መካከል፣ «ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን የህሊና ጸሎት ይቅደም» አለ።
«አይሰማም» በሚል ዓይነት፣ መልስ አላገኘም። ግን በድጋፍ መልክ ብዙ ድምጾች ተሰሙ፣ የዩኒቨርሲቲው ፖሊሶች መጡ የቻሉትን እያስነሱና መሬት ላይ እየጎተቱ አስወጡ። አምባሳደር ግርማም፣ እየተጎተታችሁ ከምትወጡ የ«አርፋችሁ ተቀመጡና አድምጡ» ማሳሰቢያ ቢያቀርቡም፣ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሰሚ ጠፋ።
በመላ አገሪቱ ከ34ሺህ የጤና ኤክስቴንሺን ባለሙያዎች ካሉበት ከጤናው ጀምሮ፣ በመንገዱ፣ በቴሌኮሚኒኬሽኑ፣ በግብርናው፣ በመልካም አስተዳደሩ፣ ወዘተረፈ ያሉትን 10 የልማትና ትራንስፎርሜሽን ግቦች፣ እንዲሁም አራት ዋና ዋና ዕቅዶች፣ እኒሁ የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ፣ ሰሌዳው ላይ በእንግሊዝኛ በተጻፈው ፓወር ፖይንት እየታገዙ፣ ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ ንግግራቸውን አቅርበዋል። በኃፊነት ባሉበት የትምህርት ዘርፍም አንዳንድ ነጥቦችን ሳያነሱ አላለፉም።
በውጭ የነበረው ተቃውሞ
በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ የክራምተን አዳራሽ ፊትለፊት በመቶዎች የተቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ ነው ያመሹት።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ ኢህአዴግ አሉታዊ ሚና ተጫውቷል ይላሉ ሰልፈኞቹ። የሙስና ጉዳይ የሚያሰጋቸው “በላባችን ያገኘንውን ገንዘብ ለስዊዝ ባንክ አንሰጥም” የሚል መፈክር አንግበው፤ የሰብዓዊ መብት የሚያሳስቧቸው ደግሞ በምርጫ 97 እና ከዚያ ወዲህ በኢህ አዴግ የተገደሉ ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ፎሮግራፎች በትላልቅ ፖስተሮች ሰቅለው ድምጻቸውን አሰምተዋል። ወደ ስብሰባው አዳራሽ የሚያመሩትን ሰዎችን በስም እየጠሩ ማሳፈር ነበረበት።
በጠቅላላው ወደ ስብሰባው አዳራሽ ለመግባት በደብዳቤ የተጠሩ ሰዎች ከቀጥር በኋላ ወደ ስብሰባው አዳራሽ መግባት ጀምረዋል።
በበር ላይ ያስተባብሩ የነበሩ ሰዎች የሚያውቋቸውን ሰዎች ያለ መጥሪያ ደብዳቤ የሞቀ-ሰላምታ ሰጥተው ሲያስገቡ፤ ሌላውን ሰው ደግሞ ደብዳቤ ሲጠይቁና ያልፈለጓቸውንና ጥሪ የነበራቸውን ሰዎች ሲመልሱ ውለዋል።
ሙሉ የሬድዮ ዘገባውን ያዳምጡ