በየመን የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር በጀመሩበት ወቅት፣ ባለፈው ኅዳር ያገቷቸውን የአንድ መኪና ጫኝ መርከብ 25 ሠራተኞች ለቀዋል።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሁቲ አማጺያን በጋዛ ተኩስ አቁም ከተጀመረ ወዲህ ውጥረቱን ለማርገብ ያደረጉት ጥረት አካል እንደሆነ ተነግሯል። ነገር ግን ፕሬዝደንት ትረምፕ፣ በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የተሰረዘውን የሽብርተኝነት ፍረጃ መልሶ እንዲፀና በማድረጋቸው አዲስ ውጥረት እንደይከሰት ተሰግቷል።
ታጋቾቹን የለቀቁት ኦማን ባደረገችው ሽምግልና ምክንያት መሆኑን የሁቲ አማጺያን አስታውቀዋል። ኦማን ከሁቲዎች ጋራ የሚደረግን ድርድር ስትሸመግል ቆይታለች፡፡ አንድ የኦማን አየር ኃይል አውሮፕላን ታጋቾቹን ከየመን ማውጣቱም ታውቋል።
በተጨማሪም 25 የሚሆኑት የመርከቡ ዓባላት እንዲለቀቁ ከሐማስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ሁቲዎቹ አስታውቀዋል። የመርከቡ ዓባላት ከፊሊፒንስ፣ ቡልጋሪያ፣ ሮማኒያ፣ ዩክሬን እና ሜክሲኮ የተውጣጡ መሆናቸውም ተመልክቷል።
“እርምጃው የተወሰደው በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ለመደገፍ ነው” ሲሉ አማጺያኑ በሚቆጣጠሩት ሳባ የዜና አገልግሎት በኩል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የፊሊፒንሱ ፕሬዝደንት ፈርዲናንድ ማርቆስ ሁለተኛ፣ 17 የሃገሪቱ ዜጎች መለቀቃቸውን አስታውቀዋል። የቡልጋሪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሁለት ዜጎቹ እንደተለቀቁ አስታውቋል።
በተመድ የየመን ልዩ ልዑክ የሆኑት ሃንስ ግረንድበርግ፣ በዘፈቀደ የታገቱ ሰዎችን ሰቆቃ ያስቆመ ነው ያሉትን እርንምጃ በመልካም ተቀብለዋል።
መድረክ / ፎረም