በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የየመን ሁቲ አማጽያን 9 የተመድ ሠራተኞችን አሠሩ


የየመን የሁቲ አማፂያን ከዘጠኝ ያላነሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችን ድንገት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አንድ የድርጅቱ ባለስልጣን ገለፁ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመንግሥታቱ ድርጅት የክልል ባለስልጣን ዛሬ ዓርብ ለአሶሴይትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ የአንድን ሰው ባለቤት ጨምሮ የታሰሩት ከዘጠኝ ያላነሱ የድርጅቱ ተቋማት ሠራተኞች ያሉበት ሁኔታ አልታወቀም፡፡

አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድንም በሁቲ በተያዙ አራት ግዛቶች ውስጥ ሌሎች የእርዳታ ሠራተኞች መታሰራቸውንም ጠቅሷል። እስሩ በእስራኤል እና በሐማስ ጦርነት ምክንያት ሁቲዎች በቀይ ባህር መርከቦችን ዒላማ በማድረግ የሚወስዱትን ጥቃት በመቃወም እየተወሰደ ያለውን ርምጃ ተከተሎ የተፈጸመ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ሁቲዎች በዩናይትድ ስቴትስ በሚመራው ኃይል በሚደርስባቸው የአየር ድብደባ እና እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑ ተገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ ሁኔታው ወዲያውኑ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም

ህጻናትን አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) የሠራተኞቹ ደህንነት ያሳሰበው መሆኑን ገልጿል።

የመብት ተሟጋቾች እና የህግ ባለሙያዎች በሁቲዎቹ የታሰሩት ግለሰቦች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ በኢንተርኔት ላይ መጻፍ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁቲዎች ከዚህ ቀደም አራት ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችን በማሰራቸው የህግ የበላይነትን ችላ ማለታቸውን አጉልቶ ያሳያል ተብሏል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ሁቲዎች በተቆጣጠሯቸው ግዛቶች ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች በሳዑዲ አረብያ እንዲከፈል ታቅዶ የነበረው 1.5 ቢሊዮን ዶላርን እንዲታገድ ማድረግን ጨምሮ፣ የገንዘብ ምንጮቻቸውን በመዝጋት፣ በሁቲዎች ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደር እያቀደች መሆኑን ብሉምበርግን ጠቅሶ አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በየመን የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከ150,000 በላይ ሰዎችን በመግደል፣ ዓለም ላይ ካሉት አስከፊ ሰብአዊ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው የተባለውን እልቂት ማስከተሉን ዘገባው ጠቅሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG