በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል መንግሥት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች


የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን አስመልክቶ ምክር ቤቱ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሦስት ናቸው።

- የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ያካሄደውን ኢ-ሕገመንግሥታዊ ምርጫ ተከትሎ ከተመሰረቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግሥት ምንም አይነት ግንኙነት እንደማያደርግ መወሰኑ ነው።

- ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ህዝብን የልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ማዕከል በማድረግ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ የሥራ ግንኙነት እንደሚያደርግ ማመልከቱ ነው።

- ሦስተኛው ደግሞ የውሳኔው አፈጻጸም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል እንዲደርግበት ውሳኔ መተላለፉ ነው።

ይህ ውሳኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ነሃሴ 30 2012 ዓ.ም አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ጉባዔ የደረሰበት ድምዳሜ ተከታይ መሆኑም ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ በዚያ ስብሰባው በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ እንዳልተደረገ፣ እንዳልተፈጸመ እና እንደማይፀና ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውሷል።

XS
SM
MD
LG