በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ


የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ
የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ

የኒውጀርሲ ክፍለ ግዛት የዲሞክራት ፓርቲ ተወካዩ ቶም ማሊኖስኪ እና ከካሊፎኒያ ክፍለ ግዛት የሪፐብሊካኑ ተወካይ ያንግ ኪም በጋራ አርቅቀው በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዕረቡ ጥር 1/2014 ዓ/ም የፀደቀው ሕግ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የእርበእርስ ጦርነት ማብቂያ ለማበጀት አስተዳደሩ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ ይጠይቃል።

በኮሚቴው ሰብሳቢ በዲሞክራት ፓርቲው አባል ግሪጎሪ ሚክስ እና በኮሚቴው የሪፐብሊካን ከፍተኛ አባል ማይክል ማኩል የተደገፈው የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሕግ የሚል ሥያሜ የተሰጠው ረቂቅ ግጭቱን "በማባባስ ላይ ባሉ" ባላቸው አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያዛል። በተጨማሪም የሰብአዊ እና የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች እስኪሟሉ ድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠው የጸጥታ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይላል።

“በኢትዮጵያ የሚካሄደው አስራ አምስት ወራት የዘለቀው ጦርነት በሲቪሎች ላይ እጅግ የከፋ ጉዳት አድርሷል” ያለው የኮሚቴው መግለጫ፣ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያጠናቀረው ሪፖርት የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እና እንዲሁም ከዘር ማጥፋት ሊቆጠር የሚችሉ ወንጀሎች ጭምር ተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ዘግቧል።” ብሏል።

ረቂቁ ህግ ሆኖ ተፈጻሚነ እንዲኖረው በምክር ቤቱ መጽደቅ ይኖርበታል።

ኮሚቴው ያሳለፈው ረቂቅ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን እንዲደግፍ ይጠይቃል፡፡

ይህም በድረ ገጽ ላይ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን መዋጋትን ጨምሮ፣ ለተፈጸሙ ግፎች ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግንና ብሔራዊ ንግግር እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት መደገፍን የሚጨምር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ውሳኔው ድርድሩን በማይቀበሉና ግጭቱ እንዳይቆም በሚፈልጉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጥቃት በሚፈጸሙ፣ ሙስናን በሚያስፋፉና ለየትኛውም ጠብ አጫሪ ወገን የጦር መሳሪያ በሚያቀብሉት ግለሰቦች ላይ ፕሬዚዳንቱ ማዕቀብ እንዲጥሉ ሥልጣን እንዲሰጣቸው ይጠይቃል፡፡ የሚደረጉ የጥቃት እንቃስቃሴዎች ቆመው ወደ ብሄራዊ ውይይት የሚያመሩ እርምጃዎች እስኪወሰዱ ፣ በግጭቱ አካባቢ ያልተገደበ የሰብአዊ ተደራሽና የሰብዓዊ ጥበቃ እስኪረጋገጥ ድረስ፣ ለኢትዮጵያ መንግሥትየ ሚሰጡ ሁሉም የደህንነትና ጸጥታ ነክ እርዳታዎች እንዲቋረጡ የሚያደርግ መሆኑም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

ለሰብዓዊ እርዳታዎች ካልሆነ በስተቀር፣ ጦርነቱን በማቆም፣ ሰላም ወደ ቦታው እንዲመለስ እስካላደረጉ ድረስ፣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መንግሥት እንደ ዓለም ባንክ ወይም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎችም ሆኑ ብድሮች እንዳይሰጡ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር እንዲቃወም የሚጠይቅ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የዩናይትድስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብዓዊ ወንጀሎች የጦር ወንጀልና ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ መካሄድ አለመካሄዱኑ መምርምሮ እንዲያሳውቅ የሚያሳስብ ረቂቅ መሆኑም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የምክርቤቱ ተወካይ ማሊኖውስኪ “የኢትዮጵያው ጦርነት በዓለም ትልቅ ሰብአዊ ቀውስ ካስከተሉ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም በውጭ ደጋፊዎቻቸው እየተረዱ ይህን ኃላፊነት የጎደለው አሰቃቂ ጥቃትና መሠረታዊ የሰብአዊ ጥሰት በመፈጸም ሁሉም ተፋላሚዎች ተጠያቂዎች ናቸው” ብለው መናገራቸውን መግለጫው አስፍሯል፡፡

በመቀጠልም ማሊኖስኪ ዛሬ “ይህ ግጭት መቆም አለበት፤ ግጭቱን የሚያራምዱቱም ተጠያቂ መሆን አለባቸው ለማለት ምክር ቤቱ አንድ ላይ ሆኗል” ብለዋል፡፡

የካሊፎርኒያው የምክር ቤት አባል ያንግ ኪም በበኩላቸው “በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው አሰቃቂው ግጭት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና መፈናቀል ተደጋጋሚ ምክንያት መሆኑን እንደቀጠለ ነው፡፡” ማለታቸው ተመልክቷል፡፡

ኪም ግጭቱን በሚያስፋፉት ላይ ማዕቀብ እንዲጣልና ግልጽ የሰብዓዊው እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር የሚያረጋግጠውን “የኢትዮጵያ የመረጋጋት የሰላምና የዴሞክራሲ በመደገፌ ኩራት ይሰማኛል” በማለት እንደሳቸው ድጋፋቸውን የሰጡትን ሌሎች የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ባልደረቦቻቸውን ጨምረው ማመስገናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

XS
SM
MD
LG